ታኅሣሥ 31, 2019
ቺሊ
የቺሊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአንዲትን ታካሚ መብት የሚያስከብር ታሪካዊ ውሳኔ አስተላለፈ
ታኅሣሥ 13, 2019 የቺሊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የበታች ፍርድ ቤት ያደረገውን ውሳኔ 3 ለ 2 በሆነ ድምፅ በመሻር አንዲት የይሖዋ ምሥክር በእምነቷ ምክንያት ደም ላለመውሰድ ያደረገችውን ውሳኔ የሚያስከብር ብይን አስተላልፏል።
ጉዳዩ እህት ፖሎኒያ ሪዮስን የሚመለከት ነው፤ ይህች እህት ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ምክንያት የሚያስፈልጋትን ቀዶ ሕክምና እንዳታገኝ በተደጋጋሚ ተከልክላ ነበር። በኋላም የሚያስፈልጋትን ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ ባልሆነው የሕዝብ ሆስፒታል ላይ ክስ መሠረተች። ነሐሴ 6, 2019 የሳን ሚጌል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የፖሎኒያን ክስ ውድቅ በማድረግ ለሆስፒታሉ ፈረደ።
ከዚያ በኋላ ግን ፖሎኒያ ወደ ቺሊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቀች ሲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ፈርዶላታል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሃይማኖታቸው ምክንያት አንድን ዓይነት ሕክምና ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ አዋቂ ታካሚዎችን መብት የሚያስከብር ውሳኔ ሲያስተላልፍ ይህ የመጀመሪያው ነው። ፍርድ ቤቱ ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት በያዘው አቋም መሠረት ሐኪሞች አንድ ሰው ሕይወቱን ለማትረፍ የሆነ ዓይነት ሕክምና መቀበል እንዳለበት ካመኑ ግለሰቡ ያንን ሕክምና ላለመቀበል መምረጥ አይችልም ነበር።
ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ብይን በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ታካሚዋ ጤናማ ሆና በሕይወት መኖር የምትፈልግ ሰው ነች፤ ደግሞም ለዚህ የሚረዳትን ቀዶ ሕክምና ለማግኘት ለሦስት ዓመታት ስትጠብቅ ቆይታለች። . . . [ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆነችው] በግብታዊነት ወይም ሐኪሞች ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውኑ እንቅፋት ለመሆን አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያለ አቋም የያዘችው በእምነቷ ምክንያት ነው፤ ደግሞም የሕሊና ነፃነትና ሰብዓዊ ክብር ያላት ሰው እንደመሆኗ መጠን አቋሟ ሊከበርላት ይገባል፤ በተለይ ደግሞ ደም ሳትወስድ ቀዶ ሕክምናውን ማድረግ እንደምትችል የሚያሳዩ ሪፖርቶች ከመኖራቸው አንጻር ውሳኔዋ ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል።”
በቺሊ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ይህን አስደናቂ ድል በማግኘታቸው በጣም ተደስተናል።—1 ቆሮንቶስ 12:26