በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰኔ 13, 2022
ቺሊ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በማፑዱንጉን ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በማፑዱንጉን ቋንቋ ወጣ

ሰኔ 5, 2022 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በማፑዱንጉን ቋንቋ ወጣ፤ የዚህ ትርጉም ኤሌክትሮኒክም ሆነ የታተመ ቅጂ መውጣቱን ያበሰረው የቺሊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጄሰን ሪድ ነው። በመላ አገሪቱ የሚገኙ በማፑዱንጉን የሚመሩ ጉባኤዎች ፕሮግራሙን በቀጥታ ስርጭት እንዲከታተሉ ተጋብዘው ነበር። ፕሮግራሙን 800 ገደማ ሰዎች ተከታትለውታል።

አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘቷ በጣም ተደስታ

አብዛኞቹ የማፑቺ ሕዝቦች የሚኖሩት በማዕከላዊና በደቡባዊ ቺሊና አርጀንቲና ነው፤ እነዚህ አገራት የሚገኙት በፓስፊክና በአትላንቲክ ውቅያኖሶች መሃል ነው። በዚህ አካባቢ ደኖች፣ እሳተ ገሞራዎች እንዲሁም የአንዲስ የተራራ ሰንሰለትና ሰፋፊ ሜዳዎች ይገኛሉ። ማፑቺዎች እንግዳ ተቀባይና ለቅዱስ ነገሮች ትልቅ አክብሮት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው።

በማፑዱንጉን የተተረጎሙ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከ1901 አንስቶ ይገኙ ነበር፤ በ1997 ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ያዘጋጀው ሙሉው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ወጣ። ይሁንና መልእክቱን በትክክል የሚያስተላልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያስፈልግ ነበር። ለምሳሌ በ1997 የተዘጋጀው ትርጉም ኢየሱስ የተሰቀለው “መስቀል” ላይ እንደሆነ ይናገራል። አዲስ ዓለም ትርጉም ግን ኢየሱስ የሞተው ቀጥ ባለ እንጨት ላይ መሆኑን ለማሳየት “ግንድ” የሚል ትርጉም ያለውን የማፑዱንጉን ቃል ተጠቅሟል።

አዲስ ዓለም ትርጉም በኤሌክትሮኒክ መልክ መውጣቱ በተገለጸበት ወቅት ፕሮግራሙ በተላለፈባቸው 23 የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ለነበሩት ተሰብሳቢዎች በሙሉ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስም የታደለ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። የቺሊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆርጅ ጎንዛሌዝ እንዲህ ብሏል፦ “የማፑቺ ሕዝቦች ቅዱስ ነገሮች ለምሳሌ የአምላክ ቃል በኤሌክትሮኒክ መልክ ሲቀርብላቸው በይዘቱ መተማመን ይከብዳቸዋል። በመሆኑም በርካታ ሰዎች በማፑዱንጉን የተዘጋጀውን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የታተመ ቅጂ ሲያገኙ ለማንበብ እንደሚጓጉ ተስፋ እናደርጋለን።”

ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከብሔራት ሁሉ’ የተውጣጡ ተጨማሪ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁና እሱን እንዲያመልኩ እንዲረዳቸው እንጸልያለን።—ኢሳይያስ 2:2