ሰኔ 28, 2024
ቼክ ሪፑብሊክ
በቼክ ሪፑብሊክ በተካሄደ የዓለም የአይስ ሆኪ ሻምፒዮና ወቅት ምሥክርነት ተሰጠ
ዓለም አቀፍ የአይስ ሆኪ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ውድድር ከግንቦት 10 እስከ 26, 2024 በቼክ ሪፑብሊክ ተካሂዶ ነበር። ኦስትራቫ እና ፕራግ በተባሉት ሁለት ከተሞች በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ወደ 800,000 የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ውድድሩ ከተካሄደባቸው ስታዲየሞች ውጭ የጽሑፍ ጋሪዎች አስቀምጠው ነበር። በዚያ ከተገኙት አበረታች ተሞክሮዎች አንዳንዶቹ ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።
ሁለት ወጣት ወንዶች ወደ አንዱ ጋሪ ቀረብ ብለው ወንድሞችን፣ ማን እንደሆኑና ምን እየሠሩ እንደሆነ ጠየቋቸው። ወንድሞችም የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያከናውኑት ሥራ እንዲሁም አሳታፊ ስለሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ኮርሳችን ገለጹላቸው። አንደኛው ወጣት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከናወነው መቼና እንዴት እንደሆነ ጠየቃቸው። ወንድሞች፣ ኮርሱን እሱ ባመቸው ቦታና ጊዜ መውሰድ እንደሚችል አስረዱት። እሱም ለማጥናት ተስማማ።
በሌላ ቀን ሦስት ሰዎች ወንድሞቻችንን አነጋገሯቸው፤ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያከናውኑት አገልግሎት ገንዘብ እንደማይከፈላቸው ሲያውቁ በጣም ተገረሙ። ከሰዎቹ አንዱ “ገንዘብ የማይከፈላችሁ ከሆነ በዚህ ሥራ በመካፈላችሁ ምን ጥቅም ታገኛላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው። ወንድሞችም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሕይወታቸው እንዴት እንደጠቀማቸውና ለወደፊት ሕይወታቸው ስለሰጣቸው ተስፋ አብራሩላቸው። አንደኛው ሰውዬ በመልሳቸው ስለተገረመ የበለጠ ማወቅ እንደሚፈልግ የገለጸ ሲሆን ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ወሰደ።
ሌላ ሰው ደግሞ በጽሑፍ ጋሪው አካባቢ ይመላለስ ነበር። በመጨረሻም ወደ ወንድሞች ቀረብ ብሎ “በእናንተ እምነትና በእኔ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?” በማለት ጠየቃቸው። ወንድሞችም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እምነት አጠር አድርገው አብራሩለት። ሰውየው በትኩረት ካዳመጠ በኋላ ለሰጡት ግልጽ ማብራሪያ ምስጋናውን ገለጸ። ወንድሞች የjw.orgን አንዳንድ ገጽታዎች እንዲሁም ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለሚያስተምራቸው ነገሮች ይበልጥ ለማወቅ በድረ ገጹ እንዴት መጠቀም እንደሚችል አሳዩት።
“የተሻለ ነገር እንደሚመጣ [የሚገልጸውን] ምሥራች” ለሚያዳምጧቸው ሁሉ በቅንዓት እየሰበኩ ያሉትን በቼክ ሪፑብሊክ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እናደንቃቸዋለን።—ሮም 10:15