መጋቢት 7, 2022
ኒው ዚላንድ
ኒው ዚላንድ ውስጥ ምሥራቹ “በሕግ የጸና” ከሆነ 75 ዓመት ሞላው
መጋቢት 2022 የይሖዋ ምሥክሮች ኒው ዚላንድ ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ከተሰጣቸው 75 ዓመት ሞላቸው። መጋቢት 7, 1947 ወንድም ናታን ሆመር ኖር፣ ወንደም ሚልተን ሄንሸል እና ወንድም ቻርልስ ክላይተን (ኒው ዚላንድ የተመደበ የመጀመሪያው በጊልያድ የሠለጠነ ሚሲዮናዊ) ወደ ኒው ዚላንድን ፓርላማ ሄደው ነበር። የመንግሥት ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና እንዳገኙ የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ለወንድሞች ሰጧቸው። የስብከቱ ሥራ ኒው ዚላንድ ውስጥ ፍሬ ማፍራቱን ቀጥሏል፤ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የሚያገለግሉ 14,500 ገደማ አስፋፊዎች አሉ።
የመንግሥቱ ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ ኒው ዚላንድ የደረሰው በ1898 ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአስፋፊዎች ቁጥር ያለማቋረጥ እድገት አያደረገ ነው። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ጽሑፎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በግልጽ የሚያስተምሩ መሆኑ ስላላስደሰታቸው የይሖዋ ምሥክሮች በሕዝቡ ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ ሞክረዋል። ጥቅምት 24, 1940 መንግሥት በሥራችን ላይ እገዳ ጣለ። ሆኖም ፓርላማው ግንቦት 8, 1941 የተጣለውን እገዳ በማሻሻል ወንድሞች መሰብሰባቸውንና መስበካቸውን እንዲቀጥሉ ፈቀደላቸው። ይሁን እንጂ መጠቀም የሚችሉት ጽሑፎቻችንን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነበር። መጋቢት 29, 1945 እገዳው ሙሉ በሙሉ ተነሳ፤ የአስፋፊዎች ቁጥርም እንደገና መጨመሩን ቀጠለ። እገዳው ከተነሳ ከሁለት ዓመት በኋላ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ቁጥር 40 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 659 ደረሰ፤ ይህም አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ነበር።
ወንድም ኖር በ1947 ባደረገው ዓለም አቀፍ የአገልግሎት ጉብኝት ወቅት ኒው ዚላንድን ጎብኝቶ ነበር። ወደ አገሪቱ ፓርላማ የሄደው በዚህ ጉዞው ወቅት ነው።
ሕጋዊ እውቅናው ከተገኘ በኋላ ሥራውን ይበልጥ በተደራጀ መንገድ ለመምራት በዌሊንግተን ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ። አንዲሁም ወንድም ሮበርት ሌዘንቢ የመጀመሪያው የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ።
ወንድም ኖር ስለ ኒው ዚላንድ በጻፈው ሪፖርት ላይ አዲሱን ቅርንጫፍ ቢሮና እያደገ ያለውን የአስፋፊዎች ቁጥር አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የተሰጣቸውን አዲስ ኃላፊነት በመወጣት ቅርንጫፍ ቢሮውን ለመደገፍና የሚሰጣቸውን መመሪያ ለመቀበል ሁሉም ፈቃደኞች ነበሩ።”
መጋቢት 8 እና 9, 1947 በዌሊንግተን ታውን ሆል እና በከሰዓት በኋላው ክፍለ ጊዜ ደግሞ በአቅራቢያው በሚገኝ የቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ በተደረገ ልዩ ስብሰባ ላይ ወንድም ኖር እና ወንድም ሄንሸል ንግግር ሰጡ። በስብሰባው ላይ 500 ገደማ ወንድሞችና እህቶች ተገኝተው ነበር።
በወቅቱ የ17 ዓመት ወጣት የነበረችው እህት ቤሪል ቶድ ስለ ስብሰባው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እንደዚያ ባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ ስገኝ የመጀመሪያዬ ነበር፤ ወንድም ኖር በስብሰባው ላይ መገኘቱ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነበር።” ወንድም ክላይድ ካንቲ የተጠመቀው በዚያ ዕለት፣ በአቅራቢያው በሚገኝ የሕዝብ መዋኛ ገንዳ ውስጥ ነው፤ ከጊዜ በኋላ የኒው ዚላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ አስተባባሪ ሆኖ አገልግሏል።
መጋቢት 10, 1947 ደግሞ ኦክላንድ ውስጥ ወንድም ኖር፣ ወንድም ሄንሸል እና ወንድም ሌንዝቢ የሚሰጡትን ንግግር ለመስማት 300 ሰዎች ተሰብስበው ነበር። ወንድም ኖር ወደፊት በኒው ዚላንድ ውስጥ ሊመዘገብ ስለሚችለው እድገት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሥራው እንደሚያድግ እርግጠኛ ነኝ፤ ተስፋ ያለው ክልል ነው።”
ወንድም ኖር የተናገረው ትክክል መሆኑ ተረጋግጧል። ኒው ዚላንድ በቀጣዮቹ ስምንት ዓመታት ውስጥ በአማካይ 18 በመቶ እድገት አሳይታለች። በ1955 የአስፋፊዎች ቁጥር 2,519 ደርሶ ነበር። በ1989 ደግሞ የአገሪቱ አስፋፊዎች ቁጥር 10,000 ደረሰ።
ይሖዋ በኒው ዚላንድ ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን ወንድሞቻችንን ስለረዳቸው እናመሰግነዋለን።—ፊልጵስዩስ 1:7