ነሐሴ 9, 2023
ናይጄርያ
በናይጄሪያ አዳዲስ የቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ሕንፃዎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ
የናይጄሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ለቲኦክራሲያዊ ሥልጠናዎች የሚያገለግሉ ሁለት አዳዲስ ሕንፃዎችን በቅርቡ ሥራ አስጀምሯል። ሕንፃዎቹ በዋነኝነት የሚያገለግሉት ለመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ነው። ይህ ትምህርት ቤት በኡሊ፣ ናይጄሪያ በሚገኘው ሕንፃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የካቲት 2023 ሲሆን በኢባዳን፣ ናይጄሪያ በሚገኘው ሕንፃ መካሄድ የጀመረው ደግሞ ሰኔ 2, 2023 ነው። ሕንፃዎቹ ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው ለተዘጋጀው ትምህርት ቤትም ያገለግላሉ።
ሁለቱም ሕንፃዎች የተገነቡት የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሾች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ ነው። እያንዳንዱ ሕንፃ አንድ የመማሪያ ክፍል፣ አንድ ቤተ መጻሕፍት እና የተማሪዎች መኖሪያን የያዘ ነው። በናይጄሪያ በየዓመቱ ከ500 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል ያመለክታሉ። ይህን ታሳቢ በማድረግም እያንዳንዱ ሕንፃ በዓመት አራት ጊዜ ተማሪዎችን እንዲቀበል ታቅዷል። ትምህርት ቤቶቹ የሚካሄዱት በምዕራብ አፍሪካ ፒጅን፣ በኢግቦ፣ በእንግሊዝኛና በዮሩባ ቋንቋዎች ነው።
በኡሊ በሚገኘው የሥልጠና ማዕከል በቅርቡ ከተደረገው የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የተመረቁ ተማሪዎች አድናቆታቸውን በደብዳቤ ገልጸዋል፤ የትምህርት ቤቱ አካባቢ ሰላማዊና ምቹ እንደሆነም ተናግረዋል። በደብዳቤው ላይ አንዲህ ብለዋል፦ “ቦታው ለመማር ምቹ ነው። አካባቢው ጸጥታ የሰፈነበት ስለሆነና መኝታ ቤቶቹ ምቹ ስለሆኑ በትምህርቱ ላይ ለማተኮር አልተቸገርንም። በትምህርት ቤቱ የነበረንን ቆይታ ወደነዋል። በማዕከሉ ውስጥ የሚያገለግሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች በማንኛውም ሰዓት የሚያስፈልገንን ሁሉ ለማሟላት ታትረው ይሠሩ ነበር። ይህም ሞቅ ያለውን ክርስቲያናዊ ፍቅር ለማጣጣም ጥሩ አጋጣሚ ሆኖልናል።”
አዲስ የተገነቡት እነዚህ የሥልጠና ማዕከላት በናይጄሪያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ‘አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጽሙ’ እንደሚያግዟቸው እርግጠኞች ነን።—2 ጢሞቴዎስ 4:5