በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በ1930ዎቹ መጀመሪያ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችና የሸክላ ማጫወቻ ይዘው

ታኅሣሥ 13, 2021
ናይጄርያ

በናይጄርያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ያሳለፏቸውን 100 ዓመታት አስታወሱ

ከ1921-2021፦ ከትንሽ ጅማሮ እስከ 400,000 አስፋፊዎች

በናይጄርያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ያሳለፏቸውን 100 ዓመታት አስታወሱ

በናይጄርያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአገሪቱ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት ለማሰብ በቅርቡ ሁለት ልዩ ዝግጅቶችን አድርገው ነበር። ታኅሣሥ 12, 2021 በናይጄርያ ያሉ ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አስቀድሞ የተቀዳን ልዩ ፕሮግራም እንዲከታተሉ ተጋበዙ፤ ፕሮግራሙ ንግግሮችንና ስለ አገሪቱ የስብከት ሥራ ታሪክ የሚያወሱ ቃለ መጠይቆችን ያካተተ ነበር። ይህ ፕሮግራም በናይጄሪያ ምልክት ቋንቋ፣ በኢግቦ፣ በኤፊክ፣ በእንግሊዝኛ፣ በዮሩባ እና በፒጅን (ምዕራብ አፍሪካ) ቋንቋዎች ተላልፏል። ከዚህ ቀደም ብሎ፣ ታኅሣሥ 10, 2021 በቅርንጫፍ ቢሮው ልዩ አውደ ርዕይ የሚታይበት ሙዚየም ተከፍቶ ነበር። በአሁኑ ወቅት ሙዚየሙ ክፍት የሆነው በናይጄርያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለሚያገለግሉ ብቻ ነው፤ ወደፊት ግን ለጎብኚዎች ክፍት ይደረጋል።

በ1948 ወንድም ዊልያም “ባይብል” ብራውን (በስተ ግራ) በአካባቢው ካሉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ሚስዮናውያን ጋር ከቅርንጫፍ ቢሮው ፊት ለፊት ቆሞ

“ድፍረት የታየባቸው 100 ዓመታት” የሚል ርዕስ ያለው ይህ አውደ ርዕይ በድፍረት የሰበኩና ጠንካራ እምነት ያሳዩ በናይጄርያ ያሉ ወንድሞችን ታሪክ ያወሳል። በአገሪቱ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በጽሑፎቻቸው ላይ የተጣለውን እገዳ፣ ሕዝቡ ያደረሰባቸውን ነቀፋና አሰቃቂ የሆነውን የእርስ በርስ ጦርነት በመቋቋም ያሳዩትን ድፍረት ጎላ አድርጎ ያሳያል። ታሪኮቹ በኦዲዮና በቪዲዮ መልክ መቅረባቸው እንዲሁም በዚያን ጊዜ የነበሩ ወንድሞች የተጠቀሙባቸው ታሪካዊ ቁሳቁሶች በአውደ ርዕዩ ላይ መካተታቸው ታሪኩን ይበልጥ ሕያው አድርጎታል። ጎብኚዎች በናይጄርያ የስብከቱን ሥራ እድገት ይኸውም ፍላጎት ያሳዩ ጥቂት ሰዎች በሌጎስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መከታተል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ከ400,000 የሚበልጡ ሰባኪዎች እስከተገኙበት እስካሁኑ ጊዜ ድረስ ያለውን ታሪክ በአውደ ርዕዩ ላይ መመልከት ይችላሉ።

በናይጄርያም ሆነ በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የናይጄርያ ወንድሞች ላለፉት 100 ዓመታት ያሳዩትን ታማኝነት በመመልከት ድፍረት ማግኘት ይችላሉ።—ዮሐንስ 16:33