ታኅሣሥ 28, 2023
ናይጄርያ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኤዶ እና በኤሳን ቋንቋዎች ወጣ
በሁለት ተከታታይ የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ የናይጄርያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአገሪቱ በሚነገሩ ሁለት ቋንቋዎች መውጣቱን አበሰሩ። የመጻሕፍቱ መውጣት የተበሰረው “በትዕግሥት ጠብቁ”! በሚል ርዕስ በቤኒን ሲቲ እና በአግቦር፣ ናይጄርያ በተካሄዱት የ2023 የክልል ስብሰባዎች ላይ ነበር። ታኅሣሥ 8, 2023 ወንድም አርቺቦንግ ኤቢቲ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በኤዶ ቋንቋ መውጣቱን ተናገረ። ታኅሣሥ 15, 2023 ላይ ደግሞ ወንድም ማልኮም ሆልስ መጽሐፉ በኤሳን ቋንቋ መውጣቱን ገለጸ። በሁለቱም ፕሮግራሞች ላይ፣ የታተሙት ቅጂዎች ለተሰብሳቢዎች ተሰጥተዋል። ተሰብሳቢዎች የመጽሐፍ ቅዱሶቹን የኤሌክትሮኒክ ቅጂና ኦዲዮ ማውረድም ችለዋል።
ኤዶ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በኤዶ ቋንቋ መውጣቱ በተበሰረበት ስብሰባ ላይ 1,678 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በዓለም ዙሪያ የኤዶ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንዳሉ ይገመታል። በናይጄርያ በሚገኙ በኤዶ ቋንቋ በሚካሄዱ 23 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ900 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ወደ ኤዶ ቋንቋ የሚተረጉም ቋሚ የትርጉም ቡድን የተቋቋመው በ2014 ነው። በዚያው ዓመት በዚህ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ መውጣት ጀመሩ።
በኤዶ ቋንቋ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቢኖሩም ለማግኘት ከባድ ከመሆናቸውም ሌላ ውድ ናቸው። ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል አብዛኞቹ የይሖዋን ስም አውጥተውታል፤ የሚጠቀሙበት ቋንቋም ጊዜ ያለፈበት ነው። ይህም የኤዶ ቋንቋ ተናጋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መረዳት ከባድ እንዲሆንባቸው አድርጓል። ይሖዋን ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ያገለገለችው የ74 ዓመቷ እህት ፔሸንስ ኢዜቭቡዋ እንዲህ ብላለች፦ “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኤዶ ቋንቋ በመውጣቱ በጣም ተደስቻለሁ። ደስታዬ ወደር የለውም!”
ኤሳን
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በኤሳን ቋንቋ መውጣቱ በተገለጸበት ስብሰባ ላይ ከ692 በላይ ሰዎች ተገኝተው ነበር። በናይጄርያ የኤሳን ቋንቋን የሚናገሩ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች አሉ። በአሁኑ ጊዜ 640 የሚሆኑ የኤሳን ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች በአገሪቱ ባሉ አሥር ጉባኤዎች ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ።
ይህ ትርጉም በኤሳን ቋንቋ የተዘጋጀው የመጀመሪያው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ነው። ይህ ትርጉም ከመውጣቱ በፊት አብዛኞቹ የኤሳን ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች የሚጠቀሙት የእንግሊዝኛውን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ነበር። አንዲት እህት በ2 ቆሮንቶስ 4:7 ላይ የሚገኘውን “ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” የሚለውን አገላለጽ በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ጥቅስ በእንግሊዝኛ ሳነበው በደንብ እንዳልገባኝ አስታውሳለሁ። በኤሳን ቋንቋ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ግን ጥቅሱ የተተረጎመው ‘እንደ ሸክላ ዕቃ ብንሆንም አምላክ ይህን ውድ አገልግሎት ሰጥቶናል’ ተብሎ ነው። አሁን ሐሳቡ ይበልጥ ግልጽ ስለሆነልኝ ልቤ በጥልቅ ተነክቷል። እንዴት ያለ ልዩ ስጦታ ነው!”
የኤዶ እና የኤሳን ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በቋንቋቸው በማግኘታቸው ተደስተናል፤ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” እንዲያገኙ እንዲረዷቸው እንጸልያለን።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4