በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከላይ፦ በአምስተርዳም የነበረው ቤቴል በ1964። ከታች፦ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓመታት ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ የቤቴል ቢሮዎች ውስጥ ሲያገለግሉ

ጥቅምት 7, 2022
ኔዘርላንድስ

የኔዘርላንድስ የመቶ ዓመት የፈተናና የድል ጉዞ

የኔዘርላንድስ የመቶ ዓመት የፈተናና የድል ጉዞ

በኔዘርላንድስ ዋና ከተማ በአምስተርዳም የተከፈተው ቅርንጫፍ ቢሮ ዘንድሮ ማለትም በ2022 መቶ ዓመት ይሞላዋል። በዚያ ያሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የማይበገር እምነትና ድፍረት የሚንጸባረቅበት ቲኦክራሲያዊ ታሪክ አስመዝግበዋል።

ምሥራቹ ኔዘርላንድስ የደረሰው በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ነበር፤ ሃይንሪክ ብሪንክሆፍ የተባለ ወጣት በዎች ታወር ሶሳይቲ እና በዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር የሚዘጋጁ ጽሑፎችን ማንበብ ጀመረ። ወዲያውኑ የተማረውን ነገር ለሌሎች ይናገር ጀመር። እነዚያ የእውነት ዘሮች ማደግ ጀመሩ። በ1920 ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ አውሮፓን በጎበኘበት ወቅት በስዊዘርላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ አቋቋመ። ይህ ቢሮ በኔዘርላንድስ የሚከናወነውን ሥራም ይከታተል ነበር። በ1921 ወንድም ራዘርፎርድ በኔዘርላንድስ የሚከናወነውን ሥራ በኃላፊነት እንዲከታተል ወንድም አድሪያን ብሎክን ሾመው። በ1922 በአምስተርዳም ቅርንጫፍ ቢሮ ተከፈተ።

ቅርንጫፍ ቢሮው ከተከፈተ በኋላ የስብከቱ ሥራ ይበልጥ የተደራጀ ሆነ። የይሖዋ አገልጋዮች ቁጥርም ጭማሪ ማሳየት ጀመረ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በአገሪቱ ውስጥ 500 ገደማ አስፋፊዎች ነበሩ።

ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ኔዘርላንድስ በናዚ ቁጥጥር ሥር ወደቀች። የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ አንዳንድ ቡድኖች የስደት ዒላማ ሆኑ። አገሪቱ በናዚ ቁጥጥር ሥር በነበረችበት ወቅት 300 ገደማ የኔዘርላንድ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሌላ ቦታ ተጋዙ፤ ከእነሱ መካከል አብዛኞቹም ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተላኩ። ከወንድሞቻችን መካከል 130 ገደማ የሚሆኑት በሕመምና በሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በዚህ የመረረ ስደት ውስጥ ቢያልፉም እንኳ ጦርነቱ በ1945 ሲያበቃ የኔዘርላንድስ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 3,125 ደርሶ ነበር።

የሚያሳዝነው፣ ጦርነቱ ያብቃ እንጂ በወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰው ፈተና ገና አላበቃም ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በተለይ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የይሖዋ ምሥክሮችን አጥብቃ ትቃወም ነበር። ለአብነት ያህል፣ በ1952 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በቬንሎ ትልቅ ስብሰባ እንዳይካሄድ ለማገድ ሞክራ ነበር። በዚህ ተቃውሞ የተነሳ የስብሰባ ቦታውን ለማከራየትና እና ሌሎች አገልግሎቶች ለመስጠት ከወንድሞች ጋር የተዋዋሉት ሰዎች ውላቸውን ሰረዙ። ወንድሞች ግን ይህ እንዲያግዳቸው አልፈቀዱም፤ ሜዳ ላይ ድንኳናቸውን ዘርግተው ትልቅ ስብሰባ አካሄዱ።

ተቃዋሚዎቹ ተስፋ አልቆረጡም። አንደኛው ቀን ላይ ፕሮግራሙን ለመበጥበጥ ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች ተሰባስበው መጡ። በእሁድ ዕለት የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ላይ ደግሞ ፖሊሶች እንኳ ሳይቀሩ መጥተው አንዳንድ ወንድሞችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ።

በኤመን የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በአሁኑ ወቅት

ተቃዋሚዎቹ ይህን ያህል ይሞክሩ እንጂ አልተሳካላቸውም። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የቅርንጫፍ ቢሮውን መመሪያ በመከተል ፕሮግራሙን ማስቀጠል ቻሉ።

ይሖዋ የወንድሞቻችንን ጽናት መባረኩን ቀጥሏል። በ1983 የኔዘርላንድስ ቅርንጫፍ ቢሮ በኤመን ወዳለው አዲስ ሕንፃ ተዛወረ። በ2022 በኔዘርላንድስ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 30,000 ገደማ ሆኗል።

የኔዘርላንድስ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ እንደሚያረጋግጠው ይሖዋ ሕዝቡን ፈጽሞ ‘የማይጥል ወይም የማይተው’ አምላክ ነው።—ዘዳግም 31:6