በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ፑሽፓ ጊሜሬ እና (በስተግራ) እና እህት ትሪያ ማያ ጌሌ (በስተቀኝ) ኅዳር 4, 2019 ከመፈታታቸው በፊት እጃቸው በካቴና ታስሮ

ኅዳር 15, 2019
ኔፓል

በኔፓል ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ የተፈረደባቸው ሁለት እህቶች ይግባኛቸው እስኪታይ ድረስ ከእስር ተለቀቁ

በኔፓል ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ የተፈረደባቸው ሁለት እህቶች ይግባኛቸው እስኪታይ ድረስ ከእስር ተለቀቁ

ኅዳር 4, 2019 ትሪያ ማያ ጌሌ እና ፑሽፓ ጊሜሬ የተባሉ ሁለት እህቶች በገደብ እንዲፈቱ ተደርጓል፤ እነዚህ እህቶች የታሰሩት አምልኳቸውን ሲያካሂዱ በመገኘታቸው ብቻ ሲሆን አምልኮ ማካሄድ በኔፓልም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ የተፈቀደ ነው። እነዚህ እህቶች፣ ከተፈረደባቸው የሦስት ወር እስራት ውስጥ ከአንድ ወር በላይ በእስር አሳልፈዋል።

እህት ጌሌ እና እህት ጊሜሬ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር በመንገድ ላይ በመወያየታቸው ምክንያት ከአንድ ዓመት በፊትም ታስረው ነበር። እነዚህ እህቶች 13 ቀናት በፖሊስ ጣቢያ ካሳለፉ በኋላ በጣም የተጋነነ መጠን ያለው ገንዘብ ይኸውም 100,000 የኔፓል ሩፒ (930 የአሜሪካ ዶላር ገደማ) የዋስትና ገንዘብ አስይዘው ከእስር ተለቅቀዋል። ሆኖም የአካባቢው ባለሥልጣናት በእህቶች ላይ የወንጀል ምርመራ ማካሄዳቸውን አላቆሙም።

ታኅሣሥ 10, 2018 የእህቶች የክስ ሂደት መሰማት የጀመረ ሲሆን ይህም ለአሥር ወራት ገደማ ቆይቷል። መስከረም 25, 2019 የሩፔንዳሂ አውራጃ ፍርድ ቤት ሁለቱም እህቶች ለሦስት ወራት እንዲታሰሩና 2,500 የኔፓል ሩፒ (23 የአሜሪካ ዶላር ገደማ) የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ በይኖባቸዋል።

የአውራጃው ፍርድ ቤት ዳኛ፣ እህቶችን ‘የሌሎችን እምነት ለማስቀየር ሞክረዋል’ በሚል የፈረደባቸው ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ይዘው በመገኘታቸውና በማሰራጨታቸው ብቻ ነው። ኔፓል የተባበሩት መንግሥታት አባል ከመሆኗም በላይ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት የፈረመች አገር ናት፤ በመሆኑም መንግሥት ዜጎቹ ሃይማኖታቸውን የመቀየር እንዲሁም እምነታቸውን በግልም ይሁን በይፋ የማካሄድ መብታቸውን የማስከበር ግዴታ አለበት። እህት ጌሌ እና እህት ጊሜሬ ሌሎች እምነታቸውን እንዲቀይሩ አላስገደዱም፤ ከዚህ ይልቅ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ሰጥተዋል። በመሆኑም የእህቶች ጠበቃ ጥቅምት 31, 2019 ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሏል። ከፍተኛው ፍርድ ቤት እህቶች የይግባኝ ሂደቱን እስር ቤት ሆነው መከታተል እንደማያስፈልጋቸው ወስኗል፤ ስለዚህ እህቶች ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔውን እስከሚያሳውቅ ድረስ ከእስር ተለቅቀዋል።

እህት ጌሌ እና እህት ጊሜሬ የፍርድ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠባበቁ ባሉበት በዚህ ጊዜ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ብርታት፣ ደስታና ሰላም እንዲሰጣቸው እንጸልያለን።—ሮም 15:13