በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የኦስሎ አውራጃ ፍርድ ቤት

ጥር 11, 2023
ኖርዌይ

የኖርዌይ የይሖዋ ምሥክሮች፣ እውቅናቸውን ለመሰረዝ የተጀመረው ሂደት እንዲቋረጥ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤት ተቀበለው

የኖርዌይ የይሖዋ ምሥክሮች፣ እውቅናቸውን ለመሰረዝ የተጀመረው ሂደት እንዲቋረጥ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤት ተቀበለው

የኖርዌይ መንግሥት እውቅናችን እንዲሰረዝ በጀመረው ሂደት ላይ ጊዜያዊ የእግድ ትእዛዝ እንዲወጣ ወንድሞች ያቀረቡትን ጥያቄ የኦስሎ አውራጃ ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 30, 2022 ተቀብሎታል። ይህ ያስፈለገው የኦስሎ እና የቪከን ግዛት አስተዳዳሪ ሃይማኖታዊ እውቅናችንን ለመሰረዝ መወሰኗን በማስታወቋ ነው። የእግዱ ትእዛዝ ጉዳያችን ችሎት ፊት ታይቶ እልባት እስኪያገኝ ድረስ እውቅናችን ባለበት እንዲቆይ ያስችላል። የልጆችና የቤተሰቦች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይህን የእግድ ትእዛዝ ለማስቀየር እየጣረ ነው።

የኖርዌይ የርቀት የትርጉም ቢሮ እና የቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤት ሕንፃ። ሕንፃው እስከ 2012 ድረስ የኖርዌይ ቅርንጫፍ ቢሮ ሆኖ አገልግሏል፤ ከዚያ በኋላ ግን በኖርዌይ የሚካሄደው ሥራ ዴንማርክ በሚገኘው የስካንዲኔቪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ሆነ

የፍርድ ቤቱ የእግድ ትእዛዝ የሚያስገኘው ጥቅም ገና ከአሁኑ እየታየ ነው፤ ለማግባት ያሰቡ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ኖርዌይ ውስጥ መንግሥት ሃይማኖታዊ አጋቢዎች አድርጎ የሚሾመው ሃይማኖቱ ሕጋዊ እውቅና ካለው ብቻ ነው። መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ እውቅና እንደሚሰርዝ ሲያሳውቅ የይሖዋ ምሥክር ሃይማኖታዊ አጋቢዎች ከመንግሥት ያገኙትን ሹመትና ሥልጣን ያጣሉ ማለት ነው። አሁን ግን ይህ ጊዜያዊ የእግድ ትእዛዝ ስላለ የይሖዋ ምሥክር አጋቢዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ማስፈጸም ይችላሉ።

ወንድም ዮርንስታ እና እህት ያስሚን ለመጋባት ያሰቡ ጥንዶች ናቸው። አስተያየታቸው ታኅሣሥ 28, 2022 ባስገባነው የጊዜያዊ እግድ ማመልከቻ ላይ ተካቷል

ወንድም አንድሬ ዮርንስታ እና እህት ያስሚን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚነኳቸው ጥንዶች መካከል ናቸው። ታኅሣሥ 28, 2022 ጊዜያዊ የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጥ በቀረበው አቤቱታ ላይ አስተያየታቸው ተካትቶ ነበር። ወንድም ዮርንስታ፣ እሱና እጮኛው አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲያጋባቸው ይህን ያህል የፈለጉበት ምክንያት ለአንዳንዶች ግር ሊል እንደሚችል ገልጿል። ሆኖም እንዲህ ሲል ምክንያቱን አብራርቷል፦ “ሰዎች ከሚያምኑበት ነገር ጋር ልዩ ትስስር አላቸው። ይህ ትስስር ሲቋረጥ የማንነትህን ክፍል ያጣህ ያህል ሆኖ ነው የሚሰማህ።”

የኖርዌይ የይሖዋ ምሥክሮች እውቅና እንዲሰረዝ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት መንግሥት ሃይማኖታዊ ድርጅት በመሆናችን የሚሰጠንን ድጎማ ከልክሎናል፤ ላለፉት ከ30 የሚበልጡ ዓመታት ይህን ድጎማ ስንቀበል ቆይተናል። መንግሥት በአገሪቱ ለሚገኙ ከ700 የሚበልጡ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ይህን የገንዘብ እርዳታ ያከፋፍላል። መንግሥት ድጎማውን በመከልከሉ ታኅሣሥ 21, 2022 የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥት ላይ የፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል።

የኖርዌይ መንግሥት ውገዳን በተመለከተ ባለን ቅዱስ ጽሑፋዊ እምነትና ልማድ ላይ ተቃውሞውን ገልጿል። አልፎ ተርፎም አስተዳዳሪዋ የይሖዋ ምሥክሮች እውቅናቸው እንዳይሰረዝ ከፈለጉ የውገዳ ሥርዓታቸውን እንዲተዉ እስከ መጠየቅ ደርሳለች። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተወሰደው እርምጃ በባለሙያ አስተያየትም ሆነ በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የተመሠረተ አይደለም።

አስተዳዳሪዋ፣ እውቅናው መሰረዙ በነፃነት ማምለክን የሚከለክል እንዳልሆነ ገልጻለች። ይሁንና ከድርጅታችን ሕጋዊ እውቅና መሰረዝ ጋር በተያያዘ መሰል ክሶችን ተመልክቶ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ይህ የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ ነፃነት የሚጥስ እርምጃ እንደሆነ ገልጿል። a

የስካንዲኔቪያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዮርገን ፔደርሰን እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት ከ130 የሚበልጡ ዓመታት ኖርዌይ ውስጥ በሰላም አምልኳቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። መሠረታዊ መብታችንና ነፃነታችን በኖርዌይ ሕገ መንግሥትም ሆነ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት የተጠበቀ ነው። የኖርዌይ ፍርድ ቤቶች ለእኛ ከፈረዱ ብይኑ የሁሉንም የኖርዌይ ዜጎች መብትና ነፃነት ይበልጥ የሚያስጠብቅ ይሆናል።”