በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 10, 2019
አልባኒያ

በአልባኒያ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ

በአልባኒያ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ደረሰ

በአልባኒያ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት 40 ዓመታት ከደረሱት ሁሉ የከፋው ነው፤ እርግጥ በዚህ አደጋ ሕይወቱን ያጣም ሆነ የተጎዳ አንድም የይሖዋ ምሥክር የለም። ያም ቢሆን 35 የሚያህሉ የወንድሞቻችን ቤቶች እንዲሁም ለስብሰባ አዳራሽነት የሚያገለግሉ 3 ሕንፃዎች ለደህንነት አስጊ በመሆናቸው አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

አልባኒያ 6.4 በተመዘገበ ርዕደ መሬት የተመታችው ኅዳር 26, 2019 ነበር። በአደጋው 51 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፤ ከ3,000 በላይ ሰዎች ተጎድተዋል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በመሬት መንቀጥቀጡ የተነሳ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወንድሞችና እህቶች ዘመዶቻቸው ጋር እንዲሁም ሌላ ጉባኤ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተጠልለዋል። የስብሰባ አዳራሾቻቸው ጉዳት በደረሰባቸው ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች በአደጋው ባልተጎዱ ሌሎች የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ እየተሰበሰቡ ነው።

አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ለአደጋ መዘጋጀት ቤተሰቡን የጠቀማቸው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የመሬት መንቀጥቀጡ እንደደረሰ ለድንገተኛ አደጋ ያዘጋጀነውን ቦርሳ ይዘን በሩጫ ከቤት ወጣን። በቦርሳችን ውስጥ የያዝናቸውን እንደ ብርድ ልብስ፣ ውኃ፣ መድኃኒትና ምግብ ያሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶች መጠቀም ችለናል። ላሳዩን ፍቅርና እንክብካቤ ይሖዋንና የበላይ አካሉን ማመስገን እንፈልጋለን።”

የወረዳ የበላይ ተመልካቾች አደጋ ወደደረሰበት ቦታ በአፋጣኝ በመሄድ ወንድሞቻችንን ማበረታታትና ለእነሱ እረኝነት ማድረግ ችለዋል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ ቤታቸው በአደጋው ጉዳት ስለደረሰበት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ሌሎችን በማበረታታት በርካታ ሰዓታት አሳልፈዋል።

በቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞችም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ጎብኝተዋል። የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው እየተካሄደ ያለውን የእርዳታ ሥራ እየተከታተለ ነው።

በአልባኒያ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጽናት እንዲችሉ እንጸልያለን። እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች የማይኖሩበትን ጊዜ በተስፋ እንጠባበቃለን።—ሮም 8:25