በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ኤሚን ምኪታርያን፣ ወንድም ጎር ሙሽካምባርያን፣ ወንድም ሚካዬል ዳቭትያን፣ ወንድም አርትሳክ ቱማንያን እና ወንድም ሆቭሃነስ ሳርግስያን በጽዳት ሥራ በመካፈል አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ሲሰጡ

ጥር 11, 2024
አርሜንያ

በአርሜንያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸው አሥር ዓመታት ተቆጠሩ

“አገራችን ካስተላለፈቻቸው በጣም ጥሩ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ዜጎች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጡበት ዝግጅት መደረጉ ነው” በማለት የአገሪቱ የአማራጭ አገልግሎት ሪፑብሊካዊ ኮሚቴ ተወካይ ተናግረዋል

በአርሜንያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸው አሥር ዓመታት ተቆጠሩ

አርሜንያ፣ ዜጎች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ ከፈቀደች ዘንድሮ ጥር 14, 2024 አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል። አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጥበት ዝግጅት፣ በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶች በመካፈል ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበት ዕድል ይሰጣል። ከሚሰጧቸው ሥራዎች መካከል የግንባታ ሥራ፣ አትክልተኝነት፣ ማኅበራዊ ድጋፍ መስጠት ወይም ሌሎች ሕዝባዊ አገልግሎቶች ይገኙበታል። ይህ አማራጭ ከተፈቀደበት ጊዜ አንስቶ ከ450 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወጣት ወንዶች በዝግጅቱ ለመጠቀም የግል ውሳኔ አድርገዋል።

ወንድም ሳሙኤል ፔትሮስያን በመናፈሻ ውስጥ አማራጭ የሲቪል አገልግሎቱን ሲያከናውን

ወንድም ሳሙኤል ፔትሮስያን በአሁኑ ጊዜ አትክልተኛ ሆኖ በመሥራት በአማራጭ የሲቪል አገልግሎት እየተካፈለ ይገኛል። እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ ስም ለማትረፍ እየሞከርኩ ነው። ለምሳሌ የተሰጠኝን ሥራ በአግባቡ ለማከናወንና በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ። በዚህም የተነሳ አለቆቼ ለእኔ ጥሩ አመለካከት አላቸው እንዲሁም ያከብሩኛል።”

ወንድም አርቱር ማርቲሮስያን ለሦስት ዓመት ያህል በሆስፒታል ውስጥ የሲቪል አገልግሎት ሰጥቷል። ያን ጊዜ መለስ ብሎ ሲያስብ እንዲህ ብሏል፦ “እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች መርዳት የምችልበት አጋጣሚ ማግኘቴ አስደስቶኛል። ይህ አጋጣሚ መልካም ባሕርያትን እንዳዳብር እንደረዳኝም ይሰማኛል። ይበልጥ ምክንያታዊ መሆንን፣ ውጥረትን በጥሩ ሁኔታ መቋቋምንና ከሌሎች ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን ተምሬአለሁ።”

ከ2014 በፊት በአርሜንያ ያሉ ወጣት ወንድሞቻችን በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ከሕሊናቸው ጋር የሚጋጭ ድርጊት ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በርከት ላሉ ዓመታት ለሚቆይ እስራት ይዳረጉ ነበር። አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን በአርሜንያ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጥበት ዝግጅት መደረጉ ስላስገኘው ጥሩ ውጤት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “መጀመሪያ ላይ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጥበት ዝግጅት እንዲኖር የቀረበውን ሐሳብ ተቃውሜ ነበር፤ ምክንያቱም ይህ ዝግጅት የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል እንዲሁም አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ተሰምቶኝ ነበር። . . . ለካስ ተሳስቼ ነበር። ከዓመታት በኋላ በግልጽ እንደታየው . . . የይሖዋ ምሥክሮች በአማራጭ የሲቪል አገልግሎት መካፈላቸው ለብሔራዊ ደህንነት የሚፈጥረው ምንም አደጋ የለም። እንዲያውም ዕድሜ ለዚህ [ዝግጅት] በተለያዩ መስኮች የሚካፈሉ ጎበዝ ሠራተኞችን አግኝተናል።”

ወንድም ስፓርታክ ሾልያን እና ወንድም አርትዮም አግባልያን በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ሲሰጡ

የአገሪቱ የአማራጭ አገልግሎት ሪፑብሊካዊ ኮሚቴ አባል የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ብለዋል፦ “በአርሜንያ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጥ ካደረግን አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል . . . በኩራት የምንናገረው ነገር ቢኖር አገራችን ካስተላለፈቻቸው በጣም ጥሩ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ዜጎች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጡበት ዝግጅት መደረጉ ነው። አማራጭ አገልግሎቶች በሚሰጡባቸው ተቋማት ላይ ያደረግነው ቋሚ ግምገማ እንደሚያሳየው በሥራው የሚካፈሉት ሰዎች ትጉ፣ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸውና ደስተኞች ናቸው። በየዓመቱ፣ የይሖዋ ምሥክሮች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት በመስጠት ለማኅበረሰቡ ላበረከቱት ትልቅ ድጋፍ የአድናቆት ደብዳቤ ይደርሰናል። የተቋሞቹ ኃላፊዎች፣ አሉን ከሚሏቸው ጎበዝ ሠራተኞች መካከል ቀዳሚዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ይናገራሉ።”

በአርሜንያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ በተደረገው ዝግጅት አማካኝነት ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲሁም ‘በመልካም ሥራቸው’ ለይሖዋ ውዳሴ ማምጣት በመቻላቸው ደስተኞች ናቸው።​—1 ጴጥሮስ 2:12