በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በ2012 ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ከታሰሩ ወንድሞች መካከል 12ቱ ጥር 2019 ከጠበቆቻቸው ጋር (መሃል ላይ)

ታኅሣሥ 9, 2019
አርሜንያ

አርሜንያ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት 22 ወንድሞችን እስር ቤት ማስገባቷ ኢፍትሐዊ እንደሆነ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ገለጸ

አርሜንያ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት 22 ወንድሞችን እስር ቤት ማስገባቷ ኢፍትሐዊ እንደሆነ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ገለጸ

ታኅሣሥ 5, 2019 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አርሜንያ በሕሊናቸው ምክንያት የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ 22 የይሖዋ ምሥክሮች እንዲታሰሩ ማድረጓ ኢፍትሐዊ እንደሆነ በአንድ ድምፅ ወሰነ። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ለእነዚህ ወንድሞች ከ267,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ የሆነ ካሳ እንዲከፈል ፈርዷል። ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች ወታደራዊ አገልግሎት ካለመስጠታቸው ጋር ለተያያዘ አቤቱታ ይህን ያህል ከፍተኛ ካሳ እንዲከፈል በይኖ አያውቅም።

በ2012 ወንድሞቻችን ወታደራዊ አገልግሎትም ሆነ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ተፈርዶባቸው ነበር። በወቅቱ በአርሜንያ ይሰጥ የነበረው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት በመከላከያ ሠራዊት የሚተዳደር በመሆኑ የሲቪል አገልግሎት ሊባል አይችልም ነበር፤ በመሆኑም ወንድሞች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው አልፈቀደላቸውም። በዚህም ምክንያት ከሁለት ወንድሞች በቀር ሌሎቹ ሁሉ እስከ 2013 ድረስ እስር ቤት ቆይተዋል። በ2013 አርሜንያ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ንክኪ የሌለው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ያዘጋጀች ከመሆኑም ሌላ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ወንድሞቻችንን ማሰሯን አቆመች።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 5 ያስተላለፈው ብይን የይሖዋ ምሥክሮች በ2017 ከሳሽ አድያን እና ሌሎች፣ ተከሳሽ አርሜንያ ለተባለው አቤቱታ ባገኙት ድል ላይ የተመሠረተ ነበር። ፍርድ ቤቱ አርሜንያ ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ይህን የ2017 ውሳኔ ስለምታውቅ ከ22ቱ ወንድሞች ጋር ስምምነት ላይ መድረስ እንደነበረባት ገልጿል። ወንድሞች ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም የአርሜንያ መንግሥት ከእነሱ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በአንድ ድምፅ ለወንድሞቻችን ፈርዶላቸዋል።

ደስ የሚለው፣ አርሜንያ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆኑ ዜጎች ጋር በተያያዘ ያላት አቋም ከ2013 ወዲህ በእጅጉ ተሻሽሏል። ወንድሞቻችን የገለልተኝነት አቋም በመያዛቸው ምክንያት አይታሰሩም ወይም ክስ አይመሠረትባቸውም። አርሜንያ ያዘጋጀችው ወታደራዊ ንክኪ የሌለው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ላለፉት ሰባት ዓመታት ለሌሎች አገሮችም ጥሩ ምሳሌ ሆኗል። ያም ቢሆን የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 5 ያስተላለፈው ብይን አርሜንያ በ2012 ዓለም አቀፋዊ ሕጎችን የሚጻረር ድርጊት በመፈጸሟ ተጠያቂ አድርጓታል።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ይህ ብይን ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ አገሮች ከባድ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ይሖዋ በአርሜንያ ለሚኖሩ ወንድሞቻችን ይህን ታላቅ ድል ስለሰጣቸው እናመሰግነዋለን። በዚህ ውሳኔ ምክንያት እንደ ቱርክ፣ ቱርክሜኒስታን፣ አዘርባጃንና ደቡብ ኮሪያ ባሉ አገሮች ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንም ወታደራዊ አገልግሎት ላለመስጠት እንዲፈቀድላቸው እንዲሁም አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት አጋጣሚ እንዲከፈትላቸው እንጸልያለን።