ሰኔ 30, 2023
አርጀንቲና
አርጀንቲና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በዊቺ ቋንቋ የወረዳ ስብሰባ ተደረገ
ግንቦት 7, 2023 አርጀንቲና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉው የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም በዊቺ ቋንቋ ተደረገ። ተሰብሳቢዎች “ሰላም ወዳዶች” በሚል ጭብጥ የተዘጋጀውን ስብሰባ ለመከታተል በታርታጋል፣ ሳልታ በሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ተገኝተው ነበር። ፕሮግራሙ በአርጀንቲና ዙሪያ ወደሚገኙ ሦስት ራቅ ያሉ አካባቢዎችም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተላልፏል። ጠቅላላው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 169 ሲሆን ሁለት ተጠማቂዎች ነበሩ።
አብዛኞቹ የዊቺ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩት በሰሜናዊ ምዕራብ አርጀንቲና እና በደቡባዊ ምሥራቅ ቦሊቪያ ነው። ከአሥር ዓመት ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሁለት ጉባኤዎች፣ ሦስት ቡድኖችና ስድስት ቅድመ ቡድኖች ተቋቁመዋል። በዚያ ከሚገኙት አስፋፊዎች መካከል 45 የሚሆኑት፣ አፋቸውን የፈቱት በዊቺ ቋንቋ ሲሆን ቋንቋውን እየተማሩ ያሉ ሌሎች በርካታ አስፋፊዎችም አሉ።
በወረዳ ስብሰባው ላይ ከተገኙት ተሰብሳቢዎች መካከል ብዙዎቹ የሚኖሩት ገለልተኛ በሆኑ ክልሎች ነው። ፓውሊኖ የተባለ አንድ አረጋዊ ወንድም የሚኖረው ከታርታጋል 455 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኝ ቦታ ነው። በስብሰባው ላይ ለመገኘት በአውቶቡስ ለ12 ሰዓት ያህል ተጉዟል። ከስብሰባው በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞቻችን ስብሰባውን በቋንቋችን ለማዘጋጀት ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ ስለባረከ እሱን ለማመስገን ቃላት ያጥረኛል።”
ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንዳንዶቹ በይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ በአካል ሲገኙ መጀመሪያቸው ነው። ዴሊያ የተባለች የዊቺ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች ሴት መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት የጀመረችው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ነው። በወረዳ ስብሰባው ላይ ለመገኘት ከሁለት ትናንሽ ልጆቿ ጋር የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ አድርጋለች። ዴሊያ በስብሰባው ላይ በአካል በመገኘቷ ከተደሰተችባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመረቻት እህት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል መገናኘት መቻሏ ነው!
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዊቺ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው በዚህ የወረዳ ስብሰባ ላይ ሲገኙ የተሰማቸው ደስታ፣ ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ‘ልዩ በሆነ መንገድ እንደሚይዛቸው’ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—መዝሙር 4:3