የካቲት 25, 2020
አርጀንቲና
የአርጀንቲና ቅርንጫፍ ቢሮ አዲስ ቤተ መዘክር ከፈተ
በቦነስ አይረስ የሚገኘው የአርጀንቲና የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ታኅሣሥ 11, 2019 አዲስ ቤተ መዘክር ከፍቷል። ቤተ መዘክሩ “በእምነታቸው ምሰሏቸው” እና “ቃልህ ለዘላለም ይኖራል” የሚል ጭብጥ ያላቸው ሁለት አውደ ርዕዮች አሉት።
“በእምነታቸው ምሰሏቸው” የሚለው አውደ ርዕይ በ1920ዎቹ አርጀንቲና እና ኡራጓይ ውስጥ የስብከቱ ሥራ በትንሹ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለው ከፍተኛ እድገት ድረስ ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ያወሳል። የዚህ ታሪካዊ አውደ ርዕይ አንዱ ልዩ ገጽታ አርጀንቲና ውስጥ ሥራችን በታደገበት ወቅት የነበረውን የወንድሞች እንቅስቃሴ የሚተርክ መሆኑ ነው። አውደ ርዕዩ፣ ባላቸው ገለልተኛ አቋም ምክንያት ብቻ ከትምህርት ቤት ስለተባረሩ የይሖዋ ምሥክር ልጆችና የረጅም ጊዜ እስር ስለተፈረደባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ይገልጻል። ከእነዚህ ታማኝ ወጣት ወንድሞች መካከል አብዛኞቹ አካላዊና ስሜታዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ቢያንስ ሦስቱ ደግሞ በእምነታቸው የተነሳ ተገድለዋል።
“ቃልህ ለዘላለም ይኖራል” በሚለው አውደ ርዕይ ላይ የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን ባለፉት መቶ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ስፓንኛ ለመተርጎም የተደረገው ጥረት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። በአውደ ርዕዩ ላይ 47 የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶች ለእይታ ቀርበዋል፤ ከእነዚህ መካከል በ1630 እንደታተመው ፌራራ መጽሐፍ ቅዱስ ያሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውና በቀላሉ የማይገኙ መጽሐፍ ቅዱሶች ይገኙበታል። የፌራራ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ከያዙት የመጀመሪያዎቹ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱሶች አንዱ ነው፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በርዕስ ገጹ ላይ መለኮታዊውን ስም ይዟል። በተጨማሪም በ1602 የታተመው የሬና ቫሌራ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ እትም በአውደ ርዕዩ ላይ ቀርቧል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚጠቀመው ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ነው። በስፓንኛ ከተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የሬና ቫሌራ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ለበርካታ ዘመናት ብዙ ሰዎች በስደት ወደ አርጀንቲና ይመጡ ስለነበር በ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደ አርጀንቲና የመጡ ስደተኞች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም በአውደ ርዕዩ ላይ ቀርበዋል። ጎብኚዎች በሃንጋሪያኛ፣ በአርመንኛ፣ በአይሪሽ ጌሊክ፣ በዕብራይስጥ፣ በእንግሊዝኛ፣ በክሮሽያኛ፣ በዌልሽ፣ በጀርመንኛ፣ በጣሊያንኛ እና በፖርቱጋልኛ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶችን መመልከት ይችላሉ።
ለእይታ ከቀረቡት መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል በ1919 በፓብሎ ቤሶን እንደተዘጋጀው ኑዌቮ ቴስታመንቶ ያሉ በአርጀንቲና የታተሙ መጽሐፍ ቅዱሶችም ይገኛሉ፤ ከዚህም ሌላ እንደ ማፑዱንጉን፣ ሞኮቪ፣ ቶባ ኮም፣ ቶባ ዴል ኦስቴ፣ ቾሮቴ፣ ዊቺ እና ፒላጋ ባሉ አገር በቀል ቋንቋዎች የተተረጎሙ ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶችም ለእይታ ቀርበዋል።
በአርጀንቲና ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግለው ወንድም ቲሞቴዎ ኮንስታንቲኖ እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች ለእይታ እንዲቀርቡ ለማድረግ የተባበሩንን በሙሉ እናመሰግናለን። ይህ ቤተ መዘክር ከአገር ውስጥም ሆነ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጉብኚዎች ለመንፈሳዊ ቅርሳችን ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር አድርጓል።”