በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመንግሥት ባለሥልጣን የሆኑት ክሎዲዮ ሮሜሮ (በስተ ግራ) የአርጀንቲና ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል ለሆነው ለወንድም ሚጌል ፑቼቲ (በስተ ቀኝ) የምሥክር ወረቀት ሲያበረክቱ

ታኅሣሥ 31, 2019
አርጀንቲና

የቦነስ አይረስ ከተማ አስተዳደር ለ2019 ብሔራት አቀፍ ስብሰባ እውቅና የሚሰጥ የምሥክር ወረቀት አበረከተ

የቦነስ አይረስ ከተማ አስተዳደር ለ2019 ብሔራት አቀፍ ስብሰባ እውቅና የሚሰጥ የምሥክር ወረቀት አበረከተ

የቦነስ አይረስ ከተማ አስተዳደር በ2019 የተካሄደው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ እንዳለው በመግለጽ ለፕሮግራሙ እውቅና ሰጠ። ታኅሣሥ 12, 2019 ከስብሰባው ጋር በተያያዘ በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የከተማው አስተዳደር ስብሰባው ያለውን ጥቅም የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ለወንድሞቻችን አበርክቷል።

ክሎዲዮ ሮሜሮ እና ፌደሪኮ ፑግሊሴ የተባሉ ሁለት ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች በቦነስ አይረስ ለሚያከናውኑት ሥራ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ክሎዲዮ ሮሜሮ እንዲህ ብለዋል፦ “ሃይማኖታዊ እሴታችሁ እንዲሁም በመካከላችሁ ያለው ሰላምና አንድነት ለማኅበረሰቡ በጎ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በምታሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስና ለሥራችሁ ባላችሁ ትጋት የተነሳ ለሃይማኖታችሁ ከፍተኛ አድናቆት አለኝ። እምነታችሁን ለሰዎች ስታስተምሩ የምታሳዩት ፍቅርና ድፍረት በጣም የሚደነቅ ነው።” ፌደሪኮ ፑግሊሴ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “በዛሬው ዕለት የተሰበሰባችሁት ‘ፍቅር ለዘላለም ይኖራል’ የሚል መልእክት ይዛችሁ ነው። ደግሞም ይህን ባሕርይ የምታሳዩት በስብሰባው ላይ ብቻ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁም ፍቅር ለማሳየት ጥረት ታደርጋላችሁ።”

ያገኘነው እውቅና ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለሰዎች ለሚያሳዩት ፍቅር ምሥክር ይሆናል። ይሁንና ፍቅር የምናሳየው በሰዎች ዘንድ እውቅና ለማትረፍ ሳይሆን አፍቃሪ ለሆነው አምላካችን ለይሖዋ ክብር ለማምጣት ነው።—1 ዮሐንስ 4:8