በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 15, 2024
አርጀንቲና

የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ስለደረሰባቸው ስደት የሚዘግብ ልዩ አውደ ርዕይ በአርጀንቲና ተከፈተ

የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ስለደረሰባቸው ስደት የሚዘግብ ልዩ አውደ ርዕይ በአርጀንቲና ተከፈተ

ሚያዝያ 3, 2024 በቦነስ አይረስ፣ አርጀንቲና በሚገኘው የሆሎኮስት ቤተ መዘክር “ወይን ጠጅ ሦስት ማዕዘን፦ የድፍረትና የጽናት ታሪክ” የተባለ ጊዜያዊ አውደ ርዕይ ተከፈተ። አውደ ርዕዩ እስከ ነሐሴ 4, 2024 ክፍት ሆኖ ይቆያል።

ከ16,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት በናዚዎች ስደት ደርሶባቸዋል። ወደ 4,500 የሚጠጉት ወደ ማጎሪያ ካምፖች የተላኩ ሲሆን 1,750 ገደማ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በካምፖቹ ውስጥ ተለይተው የሚታወቁት በደንብ ልብሳቸው ላይ በተሰፋው ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ወይን ጠጅ ምልክት ነበር።

ሦስት ክፍሎች ባሉት በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ናዚዎች በተቆጣጠሯቸው አገራት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩትን የአቋም ጽናትና የመንፈስ ጥንካሬ የሚያሳዩ ታሪካዊ ዘገባዎችና የግል ተሞክሮዎች ቀርበዋል። ጎብኚዎች በአርጀንቲና ምልክት ቋንቋ፣ በእንግሊዝኛና በስፓንኛ የተዘጋጁ የድምጽ መግለጫዎችን ማዳመጥ እንዲሁም የተለያዩ ቪዲዎችንና በስክሪን ላይ የቀረቡ መረጃዎችን መመልከት ይችላሉ። ጎብኚዎችን የሚያግዙ አስጎብኚዎችም አሉ።

በስተ ግራ፦ አንዲት አስጎብኚ ተች ስክሪን ተጠቅማ ለጎብኚዎች ስታብራራ። መሃል፦ አንዲት ጎብኚ የካምፑን የደንብ ልብስ ፎቶግራፍ ስታነሳ። በስተ ቀኝ፦ ሁለት ጎብኚዎች የድምፅ መግለጫዎችን እያዳመጡ

የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን ቢክዱ ነፃ ለመውጣት የሚያስችላቸው ሰነድ ወደ ስፓንኛ ተተርጉሞ

በአውደ ርዕዩ ላይ ናዚዎች የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት ለማስካድ ይጠቀሙበት የነበረው ሰነድ አምሳያ ቀርቧል። ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን እና ሕዝቡን መካዳቸውን በሚገልጸው በዚህ ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ በተደጋጋሚ ጫና ይደረግባቸው ነበር፤ ሰነዱን ቢፈርሙ ነፃ መውጣት ይችሉ ነበር። በሰነዱ ላይ የፈረሙት የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ጥቂት ናቸው። በአውደ ርዕዩ ላይ ጎብኚዎች፣ ራሳቸውን በዚያ በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቦታ አስቀምጠው ሁኔታው ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናቸው ለመመልከት የሚያስችላቸው ዝግጅት አለ። ጎብኚዎቹ ይህ ሰነድ የሚቀርብላቸው ሲሆን በሰንዱ ላይ እንዲፈርሙ የሚደረግባቸውን ጫና ለመቋቋም ምን ያህል ድፍረትና ቆራጥነት እንደሚጠይቅ ቆም ብለው እንዲያስቡ ይበረታታሉ።

ናዚዎች ያደረሱትን እልቂት በተመለከተ ምርምር የሚያደርጉት ፕሮፌሰር ኢዛቤል በርንስቴይን፣ አውደ ርዕዩን ከተመለከቱ በኋላ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፦ “አውደ ርዕዩ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለእምነታቸውና ትክክል ነው ብለው ላመኑበት ጎዳና ስላደረጉት ትግል ለጎብኚዎች ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል። ሰዎች ለትክክለኛ መሥፈርቶች ደንታ ቢስ በሆኑበት በዚህ ጊዜ የእነሱ ታሪክ ጠቃሚና አስፈላጊ ለሆኑት መሥፈርቶች አቋም እንድንወስድ ያበረታታናል።”

በአውደ ርዕዩ ላይ አስጎብኚ ሆነው ከሚያገለግሉት ወንድሞችና እህቶች አንዳንዶቹ

አውደ ርዕዩ ከተከፈተ ወዲህ ከ8,400 በላይ ጎብኚዎችን አስተናግዷል። በአርጀንቲና የይሖዋ ምሥክሮች ቃል አቀባይ የሆነው ወንድም ማርኮስ ዶናዲዮ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ አውደ ርዕይ፣ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የማያውቁ ሰዎች ስለ ታሪካችን እና ስለ እምነታችን የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው ያደርጋል። በአውደ ርዕዩ በጣም ተደስተናል፤ በተቻለ መጠን ብዙዎች እንደሚጎበኙት ተስፋ እናደርጋለን።”

የይሖዋ ሕዝቦች ያሳዩት ድፍረትና የአቋም ጽናት በዚህ አውደ ርዕይ ላይ በመዘከሩአመስጋኞች ነን። የእነዚህ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ምሳሌነት ‘እስከ መጨረሻው ለመጽናት’ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ እንዲያነሳሳን ምኞታችን ነው።​—1 ቆሮንቶስ 1:8