መስከረም 12, 2024
አንጎላ
በአንጎላ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኮርሳችንን ከ200 የሚበልጡ ሰዎች ተመለከቱ
ከነሐሴ 23 እስከ 28, 2024 በሉዋንዳ፣ አንጎላ 39ኛው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ተካሂዶ ነበር። በዚህ ዓመታዊ ዝግጅት ላይ ወደ 1,800 የሚጠጉ ድርጅቶች ምርቶታቸውን ለእይታ ያቀረቡ ሲሆን 100,000 ገደማ የሚሆኑ ጎብኚዎችም መጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ኤግዚቢሽን የተካፈሉ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በዘጠኝ ቋንቋዎች የሚያሳዩበት ኪዮስክ አዘጋጅተው ነበር። ወደ ኪዮስኩ የሚመጡ ሰዎች አረፍ ብለው አሳታፊ ስለሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኮርሳችን ይበልጥ ማብራሪያ ማግኘት የሚችሉበት ቦታም ነበረው። ይህ ኮርስ እንዴት እንደሚሰጥ በኤግዚቢሽኑ ላይ 227 ጊዜ ለሰዎች ያሳየን ሲሆን ከ100 የሚበልጡ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው መጥተው እንዲያነጋግሯቸው ጠይቀዋል።
አንዲት ሴት ወደ ኪዮስኩ መጥታ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ እንደምትፈልግ ስትገልጽ አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ጋበዘቻት። በውይይታቸው ወቅት ሴትየዋ ብዙ ጥያቄዎችን ያቀረበች ሲሆን በተለይ ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ተስፋ እንደሚሰጥ ጠየቀች። አሁን ከእህታችን ጋር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን ታጠናለች።
ሌላ ሴት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስተምረው ያለክፍያ መሆኑን ስታውቅ በጣም ተገረመች። ኪዮስኩ ጋ የነበረች እህት፣ ዓላማችን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማሳወቅ መሆኑን ነገረቻት። ሴትየዋ ከዚህ ቀደም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና እንደነበረ እህታችን ስታውቅ በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የተባለውን ቪዲዮ አሳየቻት። ሴትየዋ በስብሰባዎቻችን ላይ ማንኛውም ሰው መገኘት እንደሚችል ስትሰማ ተደሰተች፤ የበለጠ ማወቅ እንደምትፈልግም ገለጸች።
ከፖርቱጋል የመጣች ሴት የይሖዋ ምሥክሮችን ኤግዚቢሽኑ ላይ በማየቷ ተደሰተች። የይሖዋ ምሥክር ከሆነች ጎረቤቷ ጋር አዘውትራ እንደምትወያይ ገለጸች። “ድርጅታችሁ በጣም ያስገርመኛል፤ ስለ እናንተ ይበልጥ ማወቅ እፈልጋለሁ!” አለች። ይህች ሴት ወደ አገሯ ስትመለስ ጎረቤቷን መጽሐፍ ቅዱስ እንድታስጠናት ለመጠየቅ እንዳሰበች ገልጻለች።
በአንጎላ ያሉ ብዙዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ እንደሚፈለጉ መግለጻቸው ብሎም ይሖዋ “የሕይወትን ውኃ በነፃ” እንዲወስዱ ያቀረበላቸውን ግብዣ በደስታ እየተቀበሉ መሆኑ አስደስቶናል።—ራእይ 22:17