በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 4, 2023
አንጎላ

አዲስ ዓለም ትርጉም በንያኔካ ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም በንያኔካ ቋንቋ ወጣ

ሐምሌ 28, 2023፣ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በንያኔካ ቋንቋ ወጣ። የአንጎላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሳልቫዶር ዶሚንጎስ ይህን ዜና ያበሰረው በደቡባዊ አንጎላ፣ በዊላ አውራጃ በምትገኘው በሉባንጎ ከተማ በተደረገው “በትዕግሥት ጠብቁ”! የተሰኘ የክልል ስብሰባ ላይ ነው። በአጠቃላይ 2,621 የሚሆኑ ሰዎች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል። የታተመው የመጽሐፍ ቅዱሱ ቅጂ ለሁሉም ተሰብሳቢዎች የታደለ ሲሆን ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎችም ለተጠቃሚዎች ተለቅቀዋል።

አብዛኞቹ የንያኔካ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩት እንደ ቤንጉዌላ፣ ናሚቢ፣ ኩኒነ እና ዊላ ባሉ የአንጎላ አውራጃዎች ነው። ጽሑፎቻችን ወደ ንያኔካ የሚተረጎሙት በሉባንጎ ከተማ ባለ የርቀት የትርጉም ቢሮ ውስጥ ነው።

ቀደም ሲል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ነጠላ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በንያኔካ ቋንቋ አውጥተዋል። በዚህ ቋንቋ የወጣው የመጀመሪያው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የንያኔካ ቋንቋ የተለያዩ ቀበሌኛዎች ስላሉት የትርጉም ቡድኑ አብዛኞቹ ተናጋሪዎች የሚረዷቸውን ቃላት ለመጠቀም ጥረት አድርጓል።

የንያኔካ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሁን አዲስ የወጣውን ትርጉም ተጠቅመው ብዙዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩና እሱን እንዲያመልኩት መርዳት የሚችሉበት አጋጣሚ በማግኘታቸው በጣም ተደስተናል።—ኢሳይያስ 2:3