በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 9, 2022
አንጎላ

የማቴዎስና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍት በቾክዌ እና በኢቢንዳ ቋንቋዎች ወጡ

የማቴዎስና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍት በቾክዌ እና በኢቢንዳ ቋንቋዎች ወጡ

ታኅሣሥ 3, 2022 የአንጎላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ካምፖስ፣ የማቴዎስ እና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍት በቾክዌ እና በኢቢንዳ ቋንቋዎች መውጣታቸውን አብስሯል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በኤሌክትሮኒክ ፎርማት መውጣታቸው የተነገረው አስቀድሞ በተቀዳ ንግግር ላይ ነው፤ ንግግሩ 2,000 ገደማ ለሚሆኑ ተሰብሳቢዎች በቀጥታ ተላልፏል።

የይሖዋ ምሥክሮች በቾክዌ ቋንቋ የሚመራ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ያቋቋሙት በ2007 ነው። በአሁኑ ወቅት በአንጎላ 10 የቾክዌ ጉባኤዎች፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ደግሞ 23 ጉባኤዎች አሉ።

አንድ የቾክዌ ተርጓሚ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፦ “በቾክዌ ቋንቋ የተዘጋጁ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ። ለምሳሌ አንደኛው፣ ለመረዳት ቀላል የሆኑ አገላለጾችን ይጠቀማል፤ ሆኖም የጥቅሱን መልእክት በመቀየር በራሱ አባባል የሚያስቀምጥ ነፃ ትርጉም ነው። ሌላኛው ትርጉም ደግሞ የተሟላ በመሆኑ ከሌሎቹ ትርጉሞች የተሻለ ነው፤ ሆኖም ለመረዳት ይከብዳል። ይህን አዲስ ትርጉም ሳነብ ግን ይሖዋ የሚያነጋግረኝ ያህል ሆኖ ይሰማኛል።”

የመጀመሪያው የኢቢንዳ ቋንቋ ጉባኤ የተቋቋመው በ2014 ነው። በአሁኑ ወቅት 13 ጉባኤዎች አሉ። የማቴዎስና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍት ከመተርጎማቸው በፊት አንድም የኢቢንዳ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አልነበረም፤ ስለዚህ አስፋፊዎች በፖርቱጋልኛ የተዘጋጀውን አዲስ ዓለም ትርጉም ለመጠቀም ይገደዱ ነበር። አንድ የኢቢንዳ ትርጉም ቡድን አባል እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጊዜ ያነበብኳቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ግልጽ የሆኑልኝ አሁን ገና ነው። የዚህ ፕሮጀክት አንድ አካል መሆን ትልቅ መብት ነው። እምነቴ በጣም ተጠናክሯል።”

በቾክዌ እና በኢቢንዳ ቋንቋዎች የወጡት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደሚያቀርቧቸው እንተማመናለን።​—ያዕቆብ 4:8