ጥቅምት 18, 2023
አንጎላ
የማቴዎስ እና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍት በአንጎላ ምልክት ቋንቋ ወጡ
መስከረም 23, 2023 በተካሄደው ልዩ ፕሮግራም ላይ፣ የአንጎላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዮሐንስ ደ ያገር የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሆኑት የማቴዎስ ወንጌል እና የሐዋርያት ሥራ በአንጎላ ምልክት ቋንቋ መውጣታቸውን አብስሯል። በሉዋንዳ፣ አንጎላ በሚገኝ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ የተገኙ 1,881 ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። አዲስ የወጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከjw.org እና ከJW Library Sign Language አፕሊኬሽን ላይ ወዲያውኑ ማውረድ ተችሏል።
በአንጎላ ወደ 360,000 የሚጠጉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። በአንጎላ ምልክት ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው በ2010 ነበር። በአሁኑ ወቅት በመላዋ አንጎላ ውስጥ በአንጎላ ምልክት ቋንቋ በሚመሩ 37 ጉባኤዎች፣ 7 ቡድኖች እና አንድ ቅድመ ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉ ከ1,000 በላይ አስፋፊዎች አሉ።
በአንጎላ ምልክት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሲተረጎሙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። አንድ ወንድም የሥራ መጽሐፍን ከተመለከተ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በሥራ 8:26-30 ላይ የሚገኘውና ፊልጶስ የኢትዮጵያዊው ባለሥልጣን ሠረገላ ላይ ለመድረስ መሮጡን የሚገልጸው ዘገባ የተተረጎመበት አስደናቂ መንገድ በአገልግሎት ተግቼ መሳተፍ ያለብኝ ለምን እንደሆነ መገንዘብ እንድችል ረድቶኛል።”
እነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በአንጎላ ምልክት ቋንቋ መውጣታቸው ብዙዎች ‘ይሖዋ ፊቱን ያበራላቸው ያህል’ ፍቅሩን እንዲያጣጥሙ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ነን።—ዘኁልቁ 6:25