ጥር 22, 2024
አንጎላ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቾክዌ ቋንቋ ወጣ
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ዊንደር ጥር 13, 2024 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቾክዌ ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። ይህን ዜና ያበሰረው በሉዋንዳ፣ አንጎላ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ ነው። በአጠቃላይ 187 ወንድሞችና እህቶች በፕሮግራሙ ላይ በአካል የተገኙ ሲሆን 353,427 የሚሆኑት ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተከታትለዋል። ከእነዚህ መካከል የቾክዌ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 1,644 ወንድሞችና እህቶች ይገኙበታል። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች የዚህን ትርጉም የታተመ ቅጂ ማግኘት ችለዋል። የመጽሐፉን የኤሌክትሮኒክ ቅጂም ማውረድ ተችሏል።
በአንጎላ፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ እና በዛምቢያ ውስጥ የቾክዌ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሦስት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ ይገመታል። በአሁኑ ጊዜ በመላው አንጎላ በቾክዌ ቋንቋ በሚካሄዱ አሥር ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 462 ወንድሞችና እህቶች አሉ። በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ደግሞ በቾክዌ ቋንቋ በሚካሄዱ 21 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 734 ወንድሞችና እህቶች አሉ።
ወንድም ዊንደር የመጽሐፉን መውጣት ባበሰረበት ንግግሩ ላይ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ይሖዋ የተባለው የአምላክ ስም 237 ጊዜ እንደሚገኝ ጠቅሷል። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሮም 10:13 ‘የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል’ በማለት ይናገራል። ሆኖም በቾክዌ ቋንቋ የሚገኙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ሐሳብ በግልጽ አላስቀመጡትም። ስለዚህ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጠቀም ሰዎች በይሖዋ ስምና መዳን በማግኘት መካከል ያለውን ዝምድና እንዲያስተውሉ ለመርዳት ጓጉቻለሁ። እንዴት ያለ ልዩ ስጦታ ነው!”
በቾክዌ ቋንቋ የተዘጋጀው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ሌሎች በርካታ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ እንዲሁም እሱን በሙሉ ልባቸውና ኃይላቸው እንዲወዱት እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—ማርቆስ 12:33