በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 29, 2021
አንጎላ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኪምቡንዱ ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኪምቡንዱ ቋንቋ ወጣ

እሁድ፣ ኅዳር 21, 2021 የአንጎላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኤሪክ ራፋዬሊ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የኤሌክትሮኒክ ቅጂ በኪምቡንዱ ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። የታተመው ቅጂ በ2022 ይወጣል። አስቀድሞ የተቀረጸው ፕሮግራም 11,000 ገደማ ለሚሆኑ ሰዎች ተላልፏል።

በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አገሪቱን በቅኝ ግዛት ይገዛ የነበረው የፖርቱጋል መንግሥት በኪምቡንዱ ቋንቋና በሌሎች የአፍሪካ ቋንቋዎች መደበኛ ትምህርት እንዳይሰጥ አገደ። በዛሬው ጊዜ ግን የአንጎላ ዋና ከተማ የሆነችውን ሉዋንዳን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች የኪምቡንዱ ቋንቋን ይናገራሉ። ኪምቡንዱ ከአገሪቱ ዋና ዋና ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ወደ ኪምቡንዱ መተርጎም የጀመሩት ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነው። በኪምቡንዱ ቋንቋ የሚካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ የተቋቋመው ግን በ2008 ነው። በአሁኑ ጊዜ በኪምቡንዱ የሚካሄዱ 55 ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን 2,614 አስፋፊዎች በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላሉ።

የኪምቡንዱ የትርጉም ቡድን አባል ከቤቱ ሆኖ ሲሠራ

በጥቅሉ ሲታይ ይህ አዲስ ትርጉም ቀድሞ ከነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አንጻር ሲታይ ለመረዳት ቀላል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል በነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማቴዎስ 5:3 የተተረጎመው “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” ተብሎ ነው። አዲስ ዓለም ትርጉም ግን ይህን ጥቅስ “አምላክ እንደሚያስፈልጋቸው የተገነዘቡ ሰዎች ደስተኛ ናቸው” በማለት ተርጉሞታል።

አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የኪምቡንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ወንድሞቻችን ትልቅ በረከት እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ለግል ጥናታቸውም ሆነ በአገልግሎት ላይ ሲጠቀሙበት ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል። በዚህ ፕሮጀክት ላይ ጥቂት አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳይ እንደሆነ ይሰማኛል።”

በኪምቡንዱ የወጣው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ቋንቋ የሚሰብኩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለመርዳት በሚያደርጉት ጥረት እንደሚያግዛቸው እንተማመናለን፤ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው “የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥሮች” በቀላሉ ማስረዳት ይችላሉ።—ሉቃስ 8:10