በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥር 10, 2020
አውስትራሊያ

በአውስትራሊያ የተነሳው ሰደድ እሳት ተባብሶ ቀጥሏል

በአውስትራሊያ የተነሳው ሰደድ እሳት ተባብሶ ቀጥሏል

በአውስትራሊያ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከተመዘገበው እጅግ ከፍተኛ ሙቀት የነበረበትን ያለፈውን ዓመት ተከትሎ ሰደድ እሳቱ ተባብሶ ቀጥሏል። ከመስከረም 2019 አንስቶ በሁሉም የአውስትራሊያ ግዛቶች በተደጋጋሚ ሰደድ እሳት ተነስቷል፤ ደግሞም የእሳቱ ወቅት ገና ስላላበቃ ሁኔታው ይበልጥ መባባሱ እንደማይቀር ይጠበቃል። በባሕሩ ዳርቻና በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኙት የቪክቶሪያ እና የኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛቶች በሰደድ እሳቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከወንድሞቻችን መካከል ሕይወቱን ያጣ ወይም ጉዳት የደረሰበት ባይኖርም ብዙ ንብረት ጠፍቷል፤ ለምሳሌ ዘጠኝ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። እስካሁን ድረስ ከ700 የሚበልጡ ወንድሞች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በርካታ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ጉዳት ከደረሰበት አካባቢ ለመልቀቅ የወሰኑት ከፍተኛ መጠን ያለው ጭስ በመኖሩ ነው፤ እንዲያውም አንዳንድ ባለሙያዎች ጭሱ ለጤና እጅግ አደገኛ መሆኑን ገልጸዋል። ከተፈናቀሉት አስፋፊዎች መካከል አብዛኞቹ እሳቱ በማይደርስበት አካባቢ በሚኖሩ ዘመዶቻቸው፣ ጓደኞቻቸው ወይም በጎረቤት ጉባኤዎች ውስጥ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቤት ተጠልለዋል።

የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ቁሳዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ለመስጠት ሲል ሁለት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። ሁለት የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት አደጋው በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወንድሞቻችንን እያበረታቱና እረኝነት እያደረጉላቸው ነው። ሰደድ እሳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአካልም ሆነ በስሜት ቢዝሉም ወንድሞች ላሳዩአቸው የማያቋርጥ ክርስቲያናዊ ፍቅር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።—1 ጴጥሮስ 2:17