በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ በቀረጻ ቦታው ግንባታ ላይ ለሚካፈሉ ሰዎች አበረታች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ሲሰጥ። ከላይ በስተ ቀኝ፦ በቤት ውስጥ የቀረጻ ቦታ ላይ ቀረጻ ሲካሄድ። ከታች በስተ ቀኝ፦ በመስክ የቀረጻ ቦታ ላይ ቀረጻ ሲካሄድ

ነሐሴ 26, 2022
አውስትራሊያ

ከኢየሱስ ወንጌል ክፍል 1 ቀረጻ ጋር የተያያዘ ወቅታዊ ሪፖርት

ከኢየሱስ ወንጌል ክፍል 1 ቀረጻ ጋር የተያያዘ ወቅታዊ ሪፖርት

ነሐሴ 12, 2022 የኢየሱስ ወንጌል ክፍል 1 ቀረጻ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቅቋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቀረጻው ሁለተኛ ምዕራፍ ይቀጥላል፤ ይህ ቀረጻ ደግሞ ጥቅምት 2022 ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው ወንድሞች የኢየሱስ ወንጌል የተባለውን ቪዲዮ ቀረጻ የጀመሩት ግንቦት 20, 2022 ነው፤ ቀረጻው በአብዛኛው የተካሄደው ቤት ውስጥ በተዘጋጀ የቀረጻ ቦታ ነው። በወቅቱ ወንድሞች ከአገልግሎት ሰጪ ሕንፃዎችና ከመስክ ቀረጻ ቦታዎች ጋር የተያያዙ የመጨረሻ ማረጋገጫ ሰነዶችን እየጠበቁ ነበር። ሐምሌ 15, 2022 እነዚህ ሰነዶች ተሟሉ። ያኔ የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ የግንባታ ዲፓርትመንት ሕንፃውንና የቀረጻ ቦታውን ለአካባቢ ቪዲዮ ቡድን (RVT) ማስረከብ ቻለ። አሁን እነዚህን ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ለፊልሙ ፕሮጀክት መጠቀም ይቻላል።

ለአካባቢ ቪዲዮ ቡድኑ (RVT) የተሠራው አገልግሎት ሰጪ ሕንፃ። ሕንፃው ኩሽና፣ መመገቢያ ክፍል፣ ቢሮዎች እንዲሁም የፀጉርና የሜካፕ ስቱዲዮ አለው። ቀረጻው ላይ የሚገቡ እንስሳት በረቱ ውስጥ ይቆያሉ

ከታሪክ አንጻር በጥንቃቄ ተጠንተው የተዘጋጁትን ከ7,000 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ የሚሸፍኑትን የፊልም ቀረጻ ቦታዎች ለማዘጋጀት በአውስትራሊያና በኒው ዚላንድ ያሉ ከ500 የሚበልጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ተሳትፈዋል። የግንባታ ኮሚቴ አስተባባሪ የሆነው ወንድም ራስል ግሪጎርሴቪች ግንባታውን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም የይሖዋን እርዳታ በግልጽ ማየት ችለናል። ያከናወንናቸውን ነገሮች ማከናወን የቻልነው በይሖዋ መንፈስ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።”

የትምህርት ኮሚቴ ረዳት የሆነው ወንድም ሮናልድ ከርዛን በመጀመሪያው ምዕራፍ ቀረጻ አብዛኛው ክፍል ላይ በስፍራው ተገኝቶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞችና በቤቴል ቤተሰብ አባላት መካከል የታየው የትብብር መንፈስና ወዳጅነት በጣም አስደናቂ ነበር። ለዓመታት ከዘለቀ ዕቅድና ግንባታ በኋላ የቀረጻ ቦታዎቹ ሙሉ አገልግሎት ሲሰጡ ማየት ልዩ ስሜት ይፈጥራል። በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ያደረጉት ድጋፍ በጣም የሚያስደስት ነው። የኢየሱስን ሕይወትና ትምህርቶች የሚያሳየው ይህ ባለ 18 ክፍል ቪዲዮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ልብ እንደሚነካ እንተማመናለን።”

በክፍል 1 የመጀመሪያ ምዕራፍ ቀረጻ የመጨረሻ ቀናት ላይ የተገኘው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ እንዲህ ብሏል፦ “አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ይህን ፕሮጀክት እየባረከው እንዳለ ግልጽ ነው። ለዚህም ይሖዋን እናመሰግነዋለን፤ በተጨማሪም በቀረጻ ቦታ ግንባታና በቀረጻ ሥራ የተካፈሉትን ሁሉ ላሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና በፍቅር ላከናወኑት ሥራ ከልብ እናመሰግናቸዋለን። ይህ ልዩ ተከታታይ ቪዲዮ ብዙዎች ኢየሱስን በጥብቅ እንዲከተሉትና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ ይረዳ ዘንድ ጸሎታችን ነው።”

 

የታሪካዊ ቀረጻ ቦታው መግቢያ

ግንባታው የተጠናቀቀው የቀረጻ ቦታ የተወሰነ ክፍል ከላይ ሲታይ

በቀረጻ ቦታው ዳርቻ ላይ ያለ የበጎች ጉረኖ

የገበያ ስፍራው

መሪዎቹ ያሉበት ቦታ