በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 30, 2019
አዘርባጃን

በአዘርባጃን ታሪካዊ የክልል ስብሰባ ተደረገ

በአዘርባጃን ታሪካዊ የክልል ስብሰባ ተደረገ

ከሐምሌ 26 እስከ 28, 2019 በአዘርባጃን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በዋና ከተማዋ በባኩ በሚገኘው ዳርናጉል ሴሪሞኒ ሃውስ የሚባል አዳራሽ ውስጥ ዓመታዊ የክልል ስብሰባቸውን አደረጉ። በዚህ ዓመት በተለያዩ አገራት ትላልቅ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች የተካሄዱ ቢሆንም በባኩ የተደረገው የክልል ስብሰባም ታሪካዊ ነበር። ይህ ስብሰባ አዘርባጃን ውስጥ እስካሁን ከተደረጉ የክልል ስብሰባዎች ሁሉ ትልቁ ሲሆን በመላዋ አገሪቱ የሚገኙ በአዘርባጃኒና በሩሲያኛ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች በሙሉ በተመሳሳይ ጊዜ ሲሰበሰቡ የመጀመሪያቸው ነው።

አዘርባጃን ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች 1,500 ገደማ ብቻ ቢሆኑም በዚህ የክልል ስብሰባ ላይ ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 1,938 ነበር። የተጠማቂዎች አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ 33 ነበር። ወንድም ማርክ ሳንደርሰን በክልል ስብሰባው ላይ ንግግር ለመስጠት ወደ አዘርባጃን የመግባት ልዩ ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር። አንድ የበላይ አካል አባል በአዘርባጃን በተደረገ የክልል ስብሰባ ላይ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው። ባለሥልጣናቱ ይህን ልዩ ፈቃድ ስለሰጡን አመስጋኞች ነን።

በወንድሞችና እህቶች መካከል ያለው አንድነት ግሩም ምሥክርነት ሰጥቷል። ስብሰባው የተካሄደበት አዳራሽ ኃላፊ በስብሰባው ወቅት በወንድሞች መካከል ያለውን ሰላም፣ ፍቅርና ደግነት እንዳየ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩትን ነገር በተግባር የሚያውሉ መሆኑን እንዳስተዋለ ተናግሯል።

በአዘርባጃን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም ድረስ የሃይማኖት ነፃነታቸው የሚጣስበት ጊዜ ቢኖርም ባለሥልጣናቱ በጊዜ ሂደት ለወንድሞቻችን ተጨማሪ ነፃነት ሰጥተዋቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ኅዳር 2018 የአዘርባጃን ከተማ በሆነችው በባኩ ሙሉ ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል። ይህ እውቅና ወንድሞቻችን በዚህች ከተማ ውስጥ በነፃነት አምልኳቸውን እንዲያከናውኑ ጠንካራ ሕጋዊ መሠረት ይሰጣቸዋል።

በአዘርባጃን የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህን ታሪካዊ የክልል ስብሰባ ማድረግ መቻላቸውን ጨምሮ በቅርቡ በርካታ መልካም ውጤቶች በማግኘታቸው ተደስተናል። በአዘርባጃንም ሆነ በመላው ዓለም ‘ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ እየተከናወነ ያለውን ሥራ ይሖዋ መባረኩን እንዲቀጥል እንጸልያለን።—ፊልጵስዩስ 1:7