የካቲት 27, 2020
አዘርባጃን
በአዘርባጃን የተገኙ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ድሎች
የአዘርባጃን የይሖዋ ምሥክሮች ከሃይማኖታዊ ነፃነት ጋር በተያያዘ በአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሁለት ድሎችን አግኝተዋል። ፍርድ ቤቱ ያስተላለፋቸው እነዚህ ብይኖች በመላው አዘርባጃን የአምልኮ ነፃነታችን ይበልጥ የተረጋገጠ እንዲሆን ያስችላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ፍርድ ቤቱ በ2010 በተጀመረው ከሳሽ “ናሲሮቭ እና ሌሎች” ተከሳሽ “አዘርባጃን” እንዲሁም ከ2009 አንስቶ በተጀመረው ከሳሽ “የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበር” ተከሳሽ “አዘርባጃን” በተባሉት ጉዳዮች ላይ የካቲት 20, 2020 ብይን አስተላልፏል። ከናሲሮቭ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፣ አዘርባጃን 2010 ላይ በስብከት የተካፈሉ የይሖዋ ምሥክሮችን በተደጋጋሚ በማሰር፣ እነሱ ላይ በመፍረድና መቀጮ በመጣል የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነትን አንቀጽ 5 እና 9 (የነፃነት መብት እና የሃይማኖት ነፃነት) እንደጣሰች ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ ለእያንዳንዱ አመልካች 3,235.80 የአሜሪካ ዶላር በድምሩ 22,650.60 የአሜሪካ ዶላር የሞራል ካሳ እንዲከፈል አዟል። የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበር ከተባለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ደግሞ አዘርባጃን ወንድሞቻችን አንዳንድ ጽሑፎችን ወደ አገር ውስጥ እንዳያስገቡና እንዳያሰራጩ በመከልከል የስምምነቱን አንቀጽ 10 (ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት) እንደጣሰች ገልጿል።
በጉዳዩ ላይ ከተሳተፉት ጠበቆች አንዱ የሆነው ጄሰን ዋይዝ እንዲህ ብሏል፦ “በአዘርባጃን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትም ሆነ ለማሰራጨት ይቸገሩ ነበር። ጽሑፎቻችንን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በመከልከላችን አቤቱታችንን በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት አቅርበናል። ከዚህ ይበልጥ ብዙ አቤቱታዎች ፍርድ ቤት ለማቅረብ የተገደድነው ግን በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ በመካፈላቸው ምክንያት ተይዘው በመታሰራቸው ነው። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፋቸው ሁለት ብይኖች በአዘርባጃን ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወሳኝ ድሎች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበር ከተባለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸው ሃይማኖታዊ ጽሑፎች በሃይማኖቶች መካከል ግጭት የሚፈጥሩ ወይም ሌላ ጎጂ ውጤት የሚያስከትሉ እንዳልሆኑ ገልጿል። ከናሲሮቭ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎች በአደባባይ ማሰራጨት እንደሚቻል ተናግሯል። ፍርድ ቤቱ አዘርባጃን ውስጥ የሃይማኖት ነፃነትንና ሐሳብን የመግለጽ መብትን በማስከበሩ ደስተኞች ነን።”
ወንድም ፋሚል ናሲሮቭ እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል በአገራችን ውስጥ ብዙ ችግር ይደርስብን ነበር። በተደጋጋሚ በፖሊስ ተይዘን ከ4 እስከ 5 ሰዓታት ምርመራ ይደረግብን ነበር። አሁን ግን በይሖዋ እርዳታና በውድ ወንድሞቻችን ጥረት የተነሳ ይህ ሁሉ ቀርቶ በነፃነት መስበክ ችለናል።”
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እነዚህን ብይኖች ከማስተላለፉ በፊትም በአዘርባጃን ውስጥ ያለን የአምልኮ ነፃነት እየተሻሻለ ነበር። መንግሥት ወንድሞቻችን ጽሑፎቻችንን ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡና እንዲያሰራጩ ፈቅዷል። ከጥር 2017 ወዲህ ስብሰባ ላይ በመገኘቱ ምክንያት የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት የይሖዋ ምሥክር የለም። በአሁኑ ወቅት ባኩ ውስጥ ባሉ ሦስት የስብሰባ አዳራሾች እንዲሁም በመላው አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የግለሰብ ቤቶች ውስጥ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። ብሔራዊ የሃይማኖታዊ ማኅበራት ኮሚቴ በመባል የሚታወቀው በአዘርባጃን ውስጥ የሚገኙ ሃይማኖቶችን የሚመዘግበውና የሚቆጣጠረው መንግሥታዊ ተቋም የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበር ከ2015 ወዲህ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር እንዲሁም የክልልና የወረዳ ስብሰባዎችን ለማከናወን የመሰብሰቢያ ቦታዎችን መከራየት እንዲችሉ ፈቃድ ሰጥቷል።
እንዲህ ያሉ የፍርድ ቤት ድሎች በማግኘታችን እንዲሁም በአዘርባጃን የሚኖሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ሁሌም ስለሚደግፋቸው አምላካችንን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—መዝሙር 98:1