ጥቅምት 20, 2022
አዘርባጃን
አዘርባጃን ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውን ሴይሙር ማማዶቭን በማሰር የአ.ሰ.መ. ፍርድ ቤት ውሳኔን ተላለፈች
መስከረም 22, 2022 በአዘርባጃን የሚገኘው የጎራንቦይ አውራጃ ፍርድ ቤት በ22 ዓመቱ ወንድም ሴይሙር ማማዶቭ ላይ የዘጠኝ ወር እስራት በይኗል፤ ወንድም ይህ ፍርድ የተላለፈበት በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው። ብይኑ እንደተላለፈ ከዚያው ከፍርድ ቤት ወደ ወህኒ ተወስዷል። ይህ ውሳኔ፣ የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች (የአ.ሰ.መ.) ፍርድ ቤት ከአዘርባጃን ጋር በተያያዘ ያስተላለፋቸውን ሁለት ብይኖች በቀጥታ የሚጥስ ነው።
የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ማሜዶቭና ሌሎች እና አዘርባጃን እንዲሁም ሚኽቲዬቭና አቢሎቭ እና አዘርባጃን የሚሉትን የክስ መዝገቦች ተመልክቶ ነበር፤ ከእነዚህ ክሶች ጋር በተያያዘ ከ2019 ወዲህ በአዘርባጃን መንግሥት ላይ ፈርዷል። ሁለቱም ውሳኔዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሃይማኖት ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆን መብታቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው፤ ይህ መብት በአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 9 ላይ የተጠቀሰ መብት እንደሆነ ይታወቃል።
ሁለቱንም ውሳኔዎች ተከትሎ የአዘርባጃን መንግሥት የወንድሞቻችንን መብቶች እንደጣሰ ማመኑን እንዲሁም ለደረሰባቸው ማንኛውም ጉዳት ካሳ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጾ ነበር። አሁን በወንድም ማማዶቭ ላይ የተፈጸመው የመብት ጥሰት ግን መንግሥት የፍርድ ቤቱን ውሳኔዎች ችላ ለማለት እንደመረጠ የሚያሳዩ ናቸው።
ግንቦት 4, 2022 ሴይሙር ማማዶቭ በጎራንቦይ ክልል ወደሚገኘው የመንግሥት የጦር ሠራዊት ምልመላ ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠራ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋሙን ለባለሥልጣናቱ ካብራራ በኋላ በአማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲቀየርለት ጥያቄ አቀረበ። ባለሥልጣናቱ፣ አግባብነት ያለውን የሴይሙርን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ። ወንድም ሴይሙር ይህ ጫና ቢደርስበትም በአቋሙ ጸንቷል።
ሴይሙር በአሁኑ ወቅት በጋንጃ ከተማ ታስሮ ይገኛል። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም አዎንታዊ አመለካከት አለው። አብረውት ለታሰሩ 30 ገደማ ሰዎች ስለ እምነቱ የመናገር አጋጣሚ እንዳገኘ ነግሮናል። እንዲያውም አንዳንዶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት እንዳደረባቸው ሪፖርት አድርጓል።
የሴይሙር ጠበቃ ይግባኝ ብሏል። የጋንጃ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፍትሐዊ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍና ወንድማችን ከእስር እንዲፈታ እንደሚወስን ተስፋ እናደርጋለን።
ሴይሙር በዚህ ፈተና ውስጥ ሲያልፍ ይሖዋ ከጎኑ እንደሚሆን አንጠራጠርም።—ኢሳይያስ 43:2