ጥር 4, 2023
አዘርባጃን
አዘርባጃን ውስጥ የታሰሩት ወንድም ሮያል ካሪሞቭ እና ሴይሙር ማማዶቭ ተፈቱ
አዘርባጃን ውስጥ በእስር ላይ የነበሩት ወንድም ሮያል ካሪሞቭ እና ሴይሙር ማማዶቭ ተፈትተዋል። ሁለቱም ወንድሞች በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ እስረኞች ነበሩ።
ቀደም ሲል እንደተዘገበው አንድ የአዘርባጃን ፍርድ ቤት፣ ሴይሙር አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ላይ እንዲመደብ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎት ነበር። መስከረም 22, 2022 የጥፋተኝነት ብይን የተላለፈበት ሲሆን የዘጠኝ ወር እስራት ተፈረደበት። ይህ ብይን የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በአዘርባጃን ላይ ያስተላለፋቸውን ሁለት ውሳኔዎች በቀጥታ የሚጥስ ነው። የሴይሙር ጠበቆች ውሳኔውን ይግባኝ ብለው ነበር፤ ይህን ተከትሎም ታኅሣሥ 12, 2022 የጋንጃ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ቅጣቱ ከእስራት ወደ ገደብ እስራት እንዲቀየር ወስኗል። ሴይሙር አሁን ከእስር ቢፈታም ፍትሐዊ ያልሆነው ብይን እንዲሰረዝለት ለአዘርባጃን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አስገብቷል።
ሴይሙር እስር ቤት በነበረበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ደብዳቤዎች እንዲገቡለት አልተፈቀደለትም፤ ይሖዋ ግን የሚያስፈልገውን ድጋፍ አድርጎለታል። እንዲህ ብሏል፦ “ክሴ ከተሰማበት የመጨረሻ ችሎት በፊት ባለው ቀን፣ አንዲት ብጫቂ ወረቀት ላይ ኢያሱ 1:5, 6 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ጻፍኩ፤ ‘ከሙሴ ጋር እንደነበርኩ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ። አልጥልህም ወይም አልተውህም’ ይላል።” ይህ ጥቅስ ሴይሙር በፖሊስ ተይዞ ወደ እስር ቤት ሲወሰድ ብርታት ሆኖታል። “ይህ ጥቅስ ለእኔ የዕለት ጥቅሴ ነበር” ብሏል።
ግንቦት 30, 2022 ሮያል፣ በጋዳባይ ክልል በሚገኘው ብሔራዊ የጦር ሠራዊት ምልመላ ቢሮ ፊት እንዲቀርብ ተጠራ። ሮያል በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት እንደማይችል በመግለጽ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ላይ እንዲመደብ ጠየቀ። ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም። ሐምሌ 25, 2022 ወታደራዊ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር አዋሉት፤ ከዚያም እስከ ኅዳር 1, 2022 ድረስ በወታደራዊ እስር ቤት ውስጥ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አቆዩት። ሮያል፣ በጋዳባይ ክልል የሚገኘው ብሔራዊ የጦር ሠራዊት ምልመላ ቢሮ ላደረገው ነገር በሚመለከተው አካል እንዲጠየቅ አመልክቷል።
ሮያል እንዲህ ብሏል፦ “ከወታደራዊ እስር ቤት እንደማልለቀቅ ሲነግሩኝ ተረብሼ ነበር። ሆኖም ይህ እምነቴ የሚፈተንበት አጋጣሚ እንደሆነ ለማስታወስ ሞከርኩ።”
ሮያል በታሰረበት ወቅቱ እህቱ እንድትጠይቀው ተፈቅዶላት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ወሰደችለት፤ ሮያል እንደተናገረው በመንፈሳዊ እንዲበረታ ያስቻለው ይህ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እቆርጣለሁ። ሆኖም ልክ እንዲህ ሲሰማኝ ይሖዋ በክንዱ ገፋ ያደርገኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤና መጸለዬ አስደናቂ ሰላም ሰጥቶኛል።”
የአዘርባጃን ባለሥልጣናት በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወንድሞቻችንን ማሰራቸውን እንዲያቆሙ፣ ከዚህ ይልቅ በሌሎች አገራትም ተግባራዊ እየሆነ እንዳለው እውነተኛ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲያዘጋጁ ጸሎታችን ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2