ግንቦት 28, 2021
አዘርባጃን
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ስብሰባ ለማድረግ ያላቸውን መብት አስከበረ
ሚያዝያ 26, 2021 የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ከሳሽ “አዚዝ አሊዬቭና ሌሎች” ተከሳሽ “አዘርባጃን” ከተባለው ክስ ጋር በተያያዘ ወሳኝ ብይን አስተላለፈ። ኮሚቴው በአዘርባጃን ውስጥ ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሲፈርድና በሰላማዊ መንገድ አምልኳችንን የማከናወን መብታችንን ሲያስከብር ይህ ሦስተኛ ጊዜው ነው።
ጉዳዩ የጀመረው ፖሊሶች በዛጋታላ ክልል በሚገኘው በአሊያባድ ሰፈር ሕገወጥ ፍተሻ ባካሄዱበት ወቅት ነው። መስከረም 21, 2013 ፖሊሶች የወንድም አዚዝ አሊዬቭን ቤት ሰብረው ገቡ፤ በወቅቱ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ የጉባኤ ስብሰባ እያደረጉ ነበር። ፖሊሶቹ ቤቱን የበረበሩ ሲሆን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን አስፈራሯቸው፤ በተጨማሪም ጽሑፎቻቸውን፣ የሕግና የሕክምና ሰነዶቻቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን ወረሱ። ከዚያም ፖሊሶቹ በቦታው የነበሩትን ሁሉ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። ወደ ጣቢያ እየተጓዙ ሳሉ እህት ሃቫ አዚዞቫ የሚጥል በሽታዋ ስለተነሳባት ራሷን ሳተች። ፖሊሶቹ ይህን ሲያዩ እሷን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ተገደዱ። ሆኖም ልክ ራሷን እንዳወቀች ለወንጀል ምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደች።
በኋላም የዛጋታላ አውራጃ ፍርድ ቤት ብዙዎቹ ወንድሞችና እህቶች የ1,500 የአዘርባጃን ማናት (በወቅቱ በነበረው ምንዛሪ 1,716 የአሜሪካ ዶላር) መቀጮ እንዲከፍሉ ወሰነ። የሼኪ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም የአውራጃ ቤቱ ያደረገው ፍርደ ገምድል ውሳኔ እንዲጸና አደረገ። ወንድሞቻችን በአገሪቱ ይግባኝ ሊጠይቁ የሚችሉበት ሌላ መንገድ ስላልነበራቸው ወደ ተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ይግባኝ አሉ።
ኮሚቴው አዘርባጃን የወንድሞቻችንን የሃይማኖት ነፃነትና ያለምክንያት ያለመታሰር መብታቸውን እንደጣሰች ገልጿል። ኮሚቴው በውሳኔው ላይ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በባለሥልጣናትና በፖሊሶች እንግልት እንደደረሰባቸው ይኸውም ፖሊሶቹ ‘እንደሚያስሯቸው እንደዛቱባቸው፣ አንዳንዶቹን እንደሰደቧቸውና ሃይማኖታቸውን እንደተቹ፣ ሆኖም ያካሄዱት ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ሆነ የሚጠቀሙባቸው ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ስለፈጠሩት ችግርም ሆነ ስላደረሱት ጉዳት ምንም ነገር እንዳልነገሯቸው’ ገልጿል። በመሆኑም አዘርባጃን ለወንድሞቻችን ካሳ እንድትከፍል እንዲሁም ‘ወደፊት ተመሳሳይ የሕግ ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ በሙሉ እንድትወስድ’ ተጠይቃለች፤ ይህም “በአገሪቱ ያሉትን ሕጎች፣ ደንቦች እና/ወይም አሠራሮች ማስተካከልን ይጨምራል።”
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዘርባጃን የሚኖሩ ወንድሞቻችን በነፃነት አምልኳቸውን ማከናወንና አብረው መሰብሰብ በመቻላቸው ደስተኞች ነን። በዘመናችን ምሥራቹ በፍርድ ቤቶች ውስጥ በሕግ የጸና እንዲሆን ስለረዳን አምላካችንን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—ፊልጵስዩስ 1:7