በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥር 5, 2021
አዘርባጃን

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ በአዘርባጃን ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ በአዘርባጃን ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ታኅሣሥ 15, 2020 የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፉ ሁለት ወሳኝ ብይኖችን አስተላልፏል። ብይኖቹ የተላለፉት ከሳሽ ረሂማ ሁሴኖቫ ተከሳሽ አዘርባጃን እንዲሁም ከሳሽ ሳላዲን ማማዶቭ፣ ራሻድ ኒፍታሊዬቭ እና ሳዳገት አባሶቫ ተከሳሽ አዘርባጃን ከተባሉት ክሶች ጋር በተያያዘ ነው። ከሁለቱም ክሶች ጋር በተያያዘ ኮሚቴው፣ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን መብት እንደጣሰ የወሰነ ከመሆኑም ሌላ ወደፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር አዘርባጃን ሕጓን እንድታስተካክል ጠይቋል።

ከሳሽ ረሂማ ሁሴኖቫ ተከሳሽ አዘርባጃን ለተባለው ክስ መነሻው ይህ ነው፦ እህት ረሂማ ሁሴኖቫ ስለ እምነቷ ለሌሎች በመናገሯ ምክንያት በባኩ የሚገኙ የሕግ አካላት ታኅሣሥ 2014 በቁጥጥር ሥር አውለዋት ነበር። በኋላም የአውራጃ ፍርድ ቤቱ 1,500 የአዘርባጃን ማናት (882 የአሜሪካ ዶላር) መቀጮ እንድትከፍል ፈረደባት፤ ይህ የሆነው በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት በባኩ ሕጋዊ ፈቃድ ስላልነበረው ነው። a እህታችን ይግባኝ ብትጠይቅም የባኩ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ የአውራጃ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጸናው። በመሆኑም እህት ረሂማ ሁሴኖቫ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፋዊ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ወሰነች።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ የአዘርባጃን መንግሥት የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነትን አንቀጽ 18(1) እንደጣሰ ገልጿል። ኮሚቴው፣ አዘርባጃን ተመጣጣኝ ካሳ እንድትከፍል ወስኗል። ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ላይ እንደሚከተለው ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው፦ “[አዘርባጃን] ወደፊት ተመሳሳይ የሕግ ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ በሙሉ የመውሰድ ግዴታ አለባት፤ ይህም ሁሉም ሰው [በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት] አንቀጽ 18 ላይ ከሚገኙት መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆን በአገሪቱ ያሉትን ሕጎች፣ ደንቦች እና/ወይም አሠራሮች ማስተካከልን ይጨምራል።”

ከሳሽ ሳላዲን ማማዶቭ፣ ራሻድ ኒፍታሊዬቭ እና ሳዳገት አባሶቫ ተከሳሽ አዘርባጃን ለተባለው ክስ ደግሞ መነሻው ይህ ነው፦ ጥቅምት 2014 በጋንጃ የሚኖሩ የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በወንድም ሳላዲን ማማዶቭ ቤት ተሰብስበው ሳለ ፖሊሶች በድንገት ስብሰባውን አቋርጠው በመግባት ቤቱን ፈተሹ፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሶችንና ሌሎች ነገሮችን ወረሱ። ወንድም ሳላዲን ማማዶቭ፣ ወንድም ራሻድ ኒፍታሊዬቭ እና እህት ሳዳገት አባሶቫ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው በዚያ ከስድስት ሰዓት በላይ እንዲቆዩ ተደረጉ። ከሁለት ቀን በኋላ በጋንጃ ከተማ የኒዛሚ አውራጃ ፍርድ ቤት ፊት ቀረቡ። ፍርድ ቤቱ የተሰብሳቢዎቹ ሃይማኖት በጋንጃ ሕጋዊ ፈቃድ ያለው ሃይማኖት እንዳልሆነ በመግለጽ ስብሰባው ሕገ ወጥ እንደሆነ በየነ። ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው 2,000 የአዘርባጃን ማናት (1,176 የአሜሪካ ዶላር) መቀጮ እንዲከፍሉ ወሰነ። ሁለቱ ወንድሞችና እህታችን ለጋንጃ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉ። የሚያሳዝነው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ፣ የአውራጃ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አልቀለበሰውም። በመሆኑም ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ አቀረቡት።

ኮሚቴው፣ የአዘርባጃን መንግሥት በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አንቀጾችን እንደጣሰ በመግለጽ ለሦስቱ የይሖዋ ምሥክሮች ካሳ እንዲከፍል ወሰነ። ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ላይ እንደሚከተለው ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው፦ “[የይሖዋ ምሥክሮቹ] በግለሰብ ቤት ውስጥ ተሰብስበው አምልኳቸውን ለማካሄድ በቅድሚያ ሃይማኖታቸው የመንግሥት ፈቃድ ማግኘት ያስፈልገዋል የተባለው ለምን እንደሆነ የአውራጃ ፍርድ ቤቱ አላብራራም።” ይህ መግለጫ በአዘርባጃን የሚገኙ ወንድሞቻችን ከመንግሥት ሕጋዊ ፈቃድ ባያገኙም ለአምልኮ የመሰብሰብ መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል።

በተጨማሪም ኮሚቴው በረሂማ ሁሴኖቫ ክስ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በዚህኛው ክስ ላይም የአዘርባጃን መንግሥት በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ የሚገኙትን መብቶች ለማክበር ሲል “በአገሪቱ ያሉትን ሕጎች፣ ደንቦች እና/ወይም አሠራሮች” እንዲገመግም ጠይቋል።

የሚያስደስተው በአዘርባጃን የሚገኘው ሁኔታ ተሻሽሏል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባለሥልጣናት የወንድሞቻችንን የአምልኮ ነፃነት የሚጋፋ ነገር አድርገው አያውቁም። እነዚህ ሁለት ብይኖች በአዘርባጃን ምሥራቹ ይበልጥ በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ እንደሚያስችሉ ተስፋ እናደርጋለን።—ፊልጵስዩስ 1:7

a ኅዳር 2018 አዘርባጃን፣ በባኩ ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉ እውቅና ሰጥታለች።