የካቲት 4, 2022
አዘርባጃን
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ አዘርባጃን ውስጥ በመስበካቸው ምክንያት የታሰሩ እህቶችን መብት የሚያስከብር ውሳኔ አስተላለፈ
ኅዳር እና ታኅሣሥ 2021 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ የይሖዋ ምሥክሮችን የመስበክ መብት የሚደግፉ ሁለት ውሳኔዎችን አስተላልፏል። ሁለቱም ውሳኔዎች አዘርባጃን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች በመናገራቸው ምክንያት ከታሰሩ ሁለት እህቶች ጋር የተያያዙ ናቸው።
ኅዳር 5, 2021 የሰብዓዊ መብት ኮሚቴው እህት ማታናት ጉርባኖቫ እና እህት ሳዳት ሙራድሃሲሎቫ የመስበክ መብት እንዳላቸው የሚገልጽ ውሳኔ አስተላልፏል። ሁለቱ እህቶች ኅዳር 2014 የታሰሩት ባለሥልጣናት ማንነቱ ካልተገለጸ ግለሰብ ቅሬታ ስለደረሳቸው ነበር። እህቶች እያንዳንዳቸው 1,500 የአዘርባጃን ማናት (880 የአሜሪካ ዶላር) ተቀጥተዋል። የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው የተበየነባቸው እስር ሕጋዊ እንዳልሆነ በመግለጽ አዘርባጃን ወደፊት ተመሳሳይ ነገር እንዳይከሰት ልትከላከል እንደሚገባ አስጠንቅቋል።
የሥጋ እህትማማቾች የሆኑት ማታናት እና ሳዳት እንዲህ ብለዋል፦ “ፖሊሶቹና ዳኛው ሊያስፈራሩን ሞክረው ነበር፤ የተከሰተው ነገር ግን እንዲያውም እምነታችንን አጠናክሮታል። ይሖዋ እጁ አጭር እንዳልሆነ እንዲሁም ለአገልጋዮቹ መቼና እንዴት ጥበቃ እንደሚያደርግ እንደሚያውቅ በድጋሚ አሳይቶናል።”
ታኅሣሥ 21, 2021 በተላለፈ ተመሳሳይ ውሳኔ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው፣ በአዘርባጃን ያሉ ፖሊሶች እህት ጄራን አዚዞቫን እና እህት ጉልናዝ ኢስራፊሎቫን ማሰራቸው ሕገ ወጥ እንደሆነ ገልጿል፤ ፖሊሶች “ከሕጋዊ አድራሻቸው ውጭ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል” በሚል እነዚህን እህቶች አስረዋቸው ነበር። ኮሚቴው እህቶች እምነታቸውን ለሌሎች መናገራቸው ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳልሆነ በውሳኔው ላይ አረጋግጧል።
ኅዳር 2016 ጄራን እና ጉልናዝ አዘርባጃን ውስጥ በጎራንቦይ ክልል ያሉ ጓደኞቻቸውን ሊጠይቁ በሄዱበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ተናግረው ነበር። አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን ለፖሊሶች አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን እህቶች በዚህ የተነሳ ታሰሩ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለፍርድ ሲቀርቡ ዳኛው እህቶችን ሰላዮች ናችሁ በማለት 2,000 የአዘርባጃን ማናት (1,176 የአሜሪካ ዶላር) ቅጣት ጣለባቸው። ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን አጸደቀ። ከዚያም እህቶች ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ይግባኝ ጠየቁ።
የመስበክ መብታችንን የሚያስከብሩ ሕጋዊ ውሳኔዎች፣ ከሁሉ የላቀ ቦታ የምንሰጠውን የስብከቱን ሥራችንን በነፃነት እንድናከናውን ያግዙናል። ምሥራቹን በድፍረት በመስበክ ረገድ ግሩም ምሳሌ ከተዉት እህቶቻችን ጋር አብረን እንደሰታለን።—ማቴዎስ 10:18