በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 8, 2023
ኢትዮጵያ

የማቴዎስ መጽሐፍ በሲዳምኛ እና በወላይትኛ ቋንቋዎች ወጣ

የማቴዎስ መጽሐፍ በሲዳምኛ እና በወላይትኛ ቋንቋዎች ወጣ

ሐምሌ 23, 2023 በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ባለ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተካሄደ ልዩ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ለማ ኮይራ የምሥራች አበሰረ። መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በሲዳምኛ እና በወላይትኛ ቋንቋዎች መውጣቱን አሳወቀ። በፕሮግራሙ ላይ 1,800 ገደማ ሰዎች በአካል ተገኝተዋል፤ ተጨማሪ 12,669 ሰዎች ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በሳተላይት በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ቻናል አማካኝነት ፕሮግራሙን ተመልክተዋል። መጻሕፍቱ መውጣታቸው እንደተበሰረ ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች ለተጠቃሚዎች ተለቅቀዋል። በቀጣዮቹ ወራት ደግሞ የታተሙ ቅጂዎች ለጉባኤዎች እንደሚላኩ ይጠበቃል።

ወላይትኛ እና ሲዳምኛ በዋነኝነት በደቡባዊ ኢትዮጵያ የሚነገሩ ቋንቋዎች ናቸው። የወላይትኛ የትርጉም ቡድን የተቋቋመው በ2005 ሲሆን በ2007 ደግሞ የሲዳምኛ የትርጉም ቡድን ተቋቋመ። ሁለቱም የትርጉም ቡድኖች የቋንቋቸው ተናጋሪዎች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ በተከፈቱ የርቀት የትርጉም ቢሮዎቻቸው ውስጥ ሥራቸውን ያከናውናሉ።

ሲዳምኛ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች የማቴዎስ መጽሐፍን በማግኘታቸው ተደስተው

እርግጥ ነው፣ በሁለቱም ቋንቋዎች ከዚህ ቀደም የተዘጋጁ ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ፤ ይሁንና በቀላሉ የማይገኙ ከመሆኑም ሌላ ዋጋቸው በጣም ውድ ነው። አንድ ተርጓሚ፣ ብዙ ሲዳምኛ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች ያለባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኞቹ ጉባኤዎች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ብቻ ነው የሚኖራቸው። ስብሰባ ሲካሄድ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቀምበት የሚችለው ተናጋሪው ብቻ ነው። ስለዚህ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን ማድረግ ስንፈልግ ወደ ስብሰባ አዳራሹ መሄዳችን የግድ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው እዚያ ብቻ ነው። አሁን ግን በሲዳምኛ ቋንቋ የማቴዎስ መጽሐፍ ስለወጣልን እዚያው ቤታችን ሆነን የአምላክን ቃል ማንበብና ማጥናት እንችላለን።”

የማቴዎስ መጽሐፍ በወላይትኛ መውጣቱ ሲበሰር ወንድሞችና እህቶች በጭብጨባ ደስታቸውን ሲገልጹ

በወላይትኛ የትርጉም ቡድን ውስጥ የሚያገለግል አንድ ተርጓሚ፣ አዲስ ዓለም ትርጉም ለተዘጋጀበት በቀላሉ የሚገባ ቋንቋ ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማቴዎስ 28:19⁠ን የሚያስቀምጠው መንፈስ ቅዱስን የራሱ አካል ያለው አድርጎ ነው። በመሆኑም አገልግሎት ላይ በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን ልዩነት ማስረዳት አስቸጋሪ ነበር። አዲስ ዓለም ትርጉም ግን መንፈስ ቅዱስን ኃይል አድርጎ በመግለጽ ጥቅሱን በትክክል አስቀምጦታል። ወደ ወላይትኛ ቋንቋ የተተረጎመው ይህ የማቴዎስ መጽሐፍ በስብከቱ ሥራ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ እምነቴ ነው።”

በሲዳምኛ እና በወላይትኛ ቋንቋዎች የወጣው መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል ምሥራቹ ‘ለብሔር፣ ለነገድ እና ለቋንቋ ሁሉ’ እየተዳረሰ እንደሆነ የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።—ራእይ 14:6