በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በባታክ ቶባ መውጣቱን ሲያስተዋውቅ

ታኅሣሥ 4, 2020
ኢንዶኔዥያ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም ኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚነገሩ አራት ቋንቋዎች ተተርጉሞ ወጣ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም ኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚነገሩ አራት ቋንቋዎች ተተርጉሞ ወጣ

ኅዳር 28, 2020 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ (የታተመውና ኤሌክትሮኒክ ቅጂ) ኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚነገሩ አራት ቋንቋዎች ወጥቷል፤ እነዚህ ቋንቋዎች ባታክ ቶባ፣ ባታክ ካሮ፣ ኒያስ እና ጃቫንኛ ናቸው። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን አስቀድሞ በተቀዳ ልዩ ንግግር አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱሶቹ መውጣታቸውን አብስሯል፤ ንግግሩ በመላው ኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ደሴቶች ውስጥ ወዳሉ ጉባኤዎች በሙሉ ተላልፏል። በአጠቃላይ 41,265 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። በተጨማሪም ወንድም ጃክሰን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ኤሌክትሮኒክ ቅጂ በቅርቡ ሱንዳ በተባለ ቋንቋ እንደሚወጣ አስታውቋል።

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሊወጡ የቻሉት ተርጓሚዎች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከሦስት ዓመት ተኩል ለሚበልጥ ጊዜ ባከናወኑት ሥራ ነው። ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች፣ ከእነዚህ አራት ቋንቋዎች ቢያንስ አንዱን ይናገራሉ። በተጨማሪም ከ2,600 የሚበልጡ አስፋፊዎች በአገልግሎትና በጉባኤ ስብሰባ ላይ የሚጠቀሙት እነዚህን ቋንቋዎች ነው።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች፣ ቀደም ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ያሉትን ፊደላትና ቃላት እምብዛም አያውቋቸውም። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “በዘመናዊ ቋንቋ የተዘጋጀው ይህ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ ሁሉም ሰው በቀላሉ በሚገባው ቋንቋ ቃሉን እንዲያነብና ልቡ እንዲነካ እንደሚፈልግ ይበልጥ አረጋግጦልኛል።”

የኢንዶኔዥያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ዳንኤል ፑርኖሞ እንዲህ ብሏል፦ “ያለንበት ጊዜ አስቸጋሪ ነው፤ በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታውን ከባድ አድርጎታል። እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በተገቢው ጊዜ ላገኙት ለዚህ መንፈሳዊ ስጦታ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።”

ይሖዋ፣ ውድ ስጦታ የሆነውን ቃሉን ተጨማሪ ሰዎች እንዲያገኙ ላደረገው ዝግጅት በጣም አመስጋኞች ነን። እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሌሎች በርካታ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች እንዲያውቁ ምኞታችን ነው።—ያዕቆብ 1:17