በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድሞቻችን በኩፓንግ፣ ኢንዶኔዥያ የሚገኘውን የወንድም ኔኖሳባንን ቤት ሲጠግኑ

ሰኔ 24, 2021
ኢንዶኔዥያ

በኢንዶኔዥያ የተካሄደው የእርዳታ ሥራ የወንድማማች ፍቅርን አጠናክሯል፤ ጥሩ ምሥክርነትም ሰጥቷል

በኢንዶኔዥያ የተካሄደው የእርዳታ ሥራ የወንድማማች ፍቅርን አጠናክሯል፤ ጥሩ ምሥክርነትም ሰጥቷል

ሚያዝያ 4, 2021 የደረሰው ሴሮጃ የተባለው አውሎ ነፋስ በኢንዶኔዥያ መጠነ ሰፊ ውድመት አስከትሏል። አውሎ ነፋሱን ተከትሎ የተከናወነው የእርዳታ ሥራ የወንድሞቻችንን ቤቶች ለመጠገን ከማስቻሉም ባለፈ የወንድማማች ፍቅርን አጠናክሯል፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ይሖዋን እንዲያወድሱም አድርጓል።

ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድገው እህት ኤላ ሉድጂፓው ቤቷ ተጎድቶ የነበረ ቢሆን የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ቤቷ እንዲታደስ አድርጓል፤ እንዲህ ብላለች፦ “የምኖረው ከልጆቼ ጋር ብቻ ቢሆንም የወንድሞቼና የእህቶቼ ድጋፍ ስላልተለየኝ ብቸኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም።” እህት ዩሊያና ባውንሴሊ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “አደጋው ልክ እንደደረሰ ወንድሞች ሊረዱኝ ሲመጡ ይሖዋ በእርግጥ እንደሚያስብልኝ ከበፊቱ ይበልጥ እርግጠኛ ሆንኩ።”

የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው አባል የሆነው ወንድም ዲኪ ቶሚ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች ሲደርስላቸው ማየት በጣም ያስደስታል። ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ሲያገኙ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆኑ ስናይ ልባችን ተነካ። ይሖዋ በሚያደርግላቸው ጥበቃና እርዳታ ላይ ያላቸውን እምነት በማየታችን የእኛም እምነት ተጠናክሯል።”

ይህን በተግባር የተደገፈ ፍቅር ያስተዋሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብቻ አልነበሩም። ወንድም ማርሴል ባኑኔክ ከቤተሰቡ ጋር የሚኖረው የጎሳ ክፍፍል ባለበት አካባቢ ነው። ጎረቤቶቹ የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወሙ ነበር። ሆኖም ጎረቤቶቹ የተለያየ ጎሳ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ለወንድም ባኑኔክ ቤተሰብ እርዳታ ሲሰጡ ተመለከቱ፤ በዚህ ጊዜ አንዳንድ ጎረቤቶቹ “የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ከሰማነው በእጅጉ የተለዩ ናቸው” አሉት። ወንድም ባኑኔክ እንዲህ ብሏል፦ “ጎረቤቶቻችን በመካከላችን ያለውን ፍቅርና አንድነት ሲመለከቱ በጣም ተገረሙ። ዘመዶቻችንም የወንድማማች ማኅበሩን ደግነት ተመልክተዋል። አሁን ስለ እምነታችን ይጠይቁናል። አፍቃሪ የሆነ የወንድማማች ማኅበር ስላለን በጣም አመስጋኞች ነን!”

ወንድም ኔኖሳባን እና ቤተሰቦቹ ከተጠገነው ቤታቸው ፊት ለፊት ቆመው

በአካባቢው ያሉ ዮሲ ዱሊ ኦቱ የተባሉ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው በሚገባ የተደራጀ በመሆኑ እንዲሁም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የወጡትን የደህንነት ደንቦች በማክበሩ ‘ሊኮረጅ እንደሚገባው’ ገልጸዋል። ለአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው እንዲህ ብለዋል፦ “ለወዳጆቻችሁ ያደረጋችሁት ነገር በጣም አስደናቂ ነው። አደጋ ሲደርስባቸው እርዳታ ለመስጠት ፈጣን እርምጃ ወስዳችኋል። የእርዳታ ሥራ የምታከናውኑት በተደራጀ መንገድ ነው፤ ለሥራውም በሚገባ የታጠቃችሁ ናችሁ።”

አደጋዎች ንብረት ሊያወድሙ ቢችሉም ክርስቲያናዊ ፍቅራችንንና አንድነታችንን ፈጽሞ ሊሰብሩት አይችሉም። የተከናወነው “መልካም ሥራ” አንድነታችንን እንዳጠናከረውና ሌሎች ይሖዋን “እንዲያከብሩ” እንዳነሳሳቸው በማየታችን በእጅጉ ተደስተናል!—ማቴዎስ 5:16