በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥር 14, 2020
ኢንዶኔዥያ

በጃካርታ ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከሰተ

በጃካርታ ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከሰተ

ታኅሣሥ 31, 2019 በጃካርታ፣ ኢንዶኔዥያ ኃይለኛ ዝናብ (38 ሴንቲ ሜትር ገደማ) በጣለበት ወቅት 100 የሚያህሉ የወንድሞቻችን ቤቶች ተጥለቅልቀዋል፤ አንዳንዶቹ ቤቶች 1.5 ሜትር ድረስ በውኃ ተውጠው ነበር።

ከወንድሞቻችን መካከል በጎርፍ መጥለቅለቁ ምክንያት የሞተም ሆነ የአካል ጉዳት የደረሰበት ባይኖርም በርካታ አስፋፊዎች ለጊዜውም ቢሆን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከቤት መውጣት ባለመቻላቸው እዚያው ሆነው መጠለያ ለመፈለግ ተገደዋል። ለጉባኤ ስብሰባ የምንጠቀምባቸው አንዳንድ ሕንፃዎችም መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የጉባኤ ሽማግሌዎች የእርዳታ ሥራውን በማደራጀት እንደ ምግብና ውኃ ያሉ መሠረታዊ ነገሮች እንዲቀርቡ አድርገዋል። ከዚህም ሌላ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በአደጋው የተጎዱ አስፋፊዎችን በመጎብኘት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ ሰጥተዋቸዋል። ሁለት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች የተቋቋሙ ሲሆን ተጨማሪ እርዳታ ለማቅረብ ምን እንደሚያስፈልግ ጥናት እያደረጉ ነው።

አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ወንድሞች በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ለመገኘት ጎርፉን ማቋረጥ ቢጠበቅባቸውም የጎርፍ መጥለቅለቁ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ አላገዳቸውም። የኢንዶኔዥያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዳንኤል ፑርኖሞ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ አደጋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በጃካርታ ከደረሱት የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋዎች የከፋው ቢሆንም ወንድሞቻችንን ተስፋ አላስቆረጣቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ በመረዳዳት ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዲያሳዩ አነሳስቷቸዋል።”

የተፈጥሮ ኃይሎች በሰዎች ላይ ጉዳት የማያስከትሉበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።—ማርቆስ 4:39