ሰኔ 6, 2022
ኢንዶኔዥያ
የማቴዎስ እና የማርቆስ ወንጌል በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ ወጣ
ግንቦት 29, 2022 የማቴዎስ እና የማርቆስ ወንጌል በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ መውጣቱን የኢንዶኔዥያ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዳኔል ፑርኖሞ አብስሯል። የእነዚህ መጻሕፍት የኤሌክትሮኒክ ቅጂ እንደወጣ የተገለጸው አስቀድሞ በተቀረጸ ፕሮግራም አማካኝነት ሲሆን 2,127 ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች በኢንዶኔዥያ የመጀመሪያውን የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ያቋቋሙት መስከረም 14, 2007 ነበር፤ ይህ ጉባኤ የተቋቋመው በሱማትራ በምትገኘው በጃምቢ ከተማ ነው። ከዚያም በ2011 እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ?፣ አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ እና የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ! የተባሉትን ሦስት ጽሑፎች በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ አወጡ። በ2011 በአገሪቱ የመጀመሪያው የምልክት ቋንቋ ወረዳ ተቋቋመ፤ ይህ ወረዳ 3,000 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን አካባቢ የሚሸፍን ነበር። በኢንዶኔዥያ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎቻችን ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱ በ2015 የርቀት የትርጉም ቢሮ ተቋቋመ። በአሁኑ ወቅት በኢንዶኔዥያ 12 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች እንዲሁም 28 ቡድኖችና ቅድመ ቡድኖች አሉ።
የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌሎች በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ የተተረጎሙ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ናቸው። ወንድም ፑርኖሞ የእነዚህን መጻሕፍት መውጣት ባበሰረበት ንግግር ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እነዚህ መጻሕፍት የተተረጎሙበት መንገድ በጣም ግሩም ነው፤ ስሜቱን በደንብ አድርገው የሚገልጹ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ባለታሪኮች በዓይነ ሕሊና መመልከት ቀላል እንዲሆን የሚያደርጉ ምልክቶች ተጠቅመዋል።”
ከተርጓሚዎቹ አንዱ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ትርጉም ስለ ኢየሱስ ይበልጥ ማወቅ እንድችል ይረዳኛል፤ ኢየሱስን እያነጋገርኩት ያለሁ ያህል ነው የተሰማኝ።”
ይህ አዲስ ትርጉም፣ የኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ ተጠቃሚዎች የአምላክን ቃል ‘ለእግራቸው መብራት፣ ለመንገዳቸውም ብርሃን’ አድርገው እንዲያዩት ይረዳቸው ዘንድ ጸሎታችን ነው።—መዝሙር 119:105