በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከትምህርት ቤት የተባረሩት የ7፣ የ10 እና የ12 ዓመት ልጆች ከቤተሰባቸው ጋር

ጥቅምት 30, 2019
ኢንዶኔዥያ

የኢንዶኔዥያ ፍርድ ቤት የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ ነፃነት አስከበረ

የኢንዶኔዥያ ፍርድ ቤት የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ ነፃነት አስከበረ

ነሐሴ 8, 2019 የሳማሪንዳ አስተዳደር ፍርድ ቤት ለባንዲራ ሰላምታ ባለመስጠታቸውና ብሔራዊ መዝሙር ባለመዘመራቸው ምክንያት ከትምህርት ቤት ለተባረሩ ሦስት ልጆች ፈረደ። ፍርድ ቤቱ ተማሪዎቹ መባረር እንዳልነበረባቸው የገለጸ ከመሆኑም ሌላ ሦስቱም ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ አዘዘ። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የኢንዶኔዥያ ወላጆች ለልጆቻቸው ሃይማኖታዊ ትምህርት የማስተማር መብት እንዳላቸውና ልጆችም በተማሩት መሠረት በመኖራቸው ምክንያት ሊቀጡ እንደማይገባ የሚያረጋግጥ ነው።

የ7 ዓመቱ ዮናታን፣ የ10 ዓመቱ ዮሱዋ እና የ12 ዓመቷ ማሪያ ከትምህርት ቤት የተባረሩት ታኅሣሥ 2018 ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ልጆቹ በብሔራዊ ዝግጅቶች ላይ አለመካፈላቸው ሕገ መንግሥቱንም ሆነ ማንኛውንም ሕግ እንደማይጥስ ብሎም ለአገራቸው ባሕልና ሰንደቅ ዓላማ አክብሮት እንደጎደላቸው የሚያሳይ እንዳልሆነ ገልጿል።

ፍርድ ቤቱ የተማሪዎቹን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት የሚያከብር እንዲሁም ልጆቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያስችል ውሳኔ በማስተላለፉ ደስተኞች ነን። ይህ ውሳኔ በኢንዶኔዥያ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው ያሉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክር ልጆችንም እንደሚጠቅም ተስፋ እናደርጋለን።