ኅዳር 24, 2023
ኢኳዶር
በኢኳዶር በተካሄደ ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ እጅግ ጥንታዊ ሆኖም ለዘመናችን የሚጠቅም መጽሐፍ ተዋወቀ
ከመስከረም 20 እስከ 24, 2023 በጓያኪል፣ ኢኳዶር ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተካሂዶ ነበር። በጓያኪል ኤክስፖፕላዛ በተካሄደው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከ30,000 የሚበልጡ ሰዎች ተገኝተዋል። ወንድሞቻችን በአውደ ርዕዩ ላይ “እጅግ ጥንታዊ ሆኖም ለዘመናችን የሚጠቅም መጽሐፍ” በሚል ትኩረት የሚስብ ጭብጥ የጽሑፎች ማሳያ አዘጋጅተው ነበር። ጭብጡ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚሰጠውን ጠቃሚ ምክር የሚያጎላ ነው። ጎብኚዎች ጽሑፎችን በስፓንኛ፣ በቻይንኛ ማንዳሪን፣ በእንግሊዝኛ፣ በኪችዋ (ኢምባቡራ)፣ በኪችዋ (ኪምቦራዞ) እና በፖርቱጋልኛ ማግኘት ይችሉ ነበር። በአውደ ርዕዩ ላይ 150 የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ተሳትፈዋል። ከ700 የሚበልጡ የታተሙ ጽሑፎች ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተሰጥተዋል፤ እንዲሁም በርካታ ጎብኚዎች jw.org ላይ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን መፈለግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አይተዋል።
አንድ አባት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቹ ጋር ወደ ጽሑፍ ማሳያችን መጥቶ ልጆቹ እያጋጠማቸው ያለው ፈተና በጣም እንደሚያሳስበው ተናገረ። በዚህ ጊዜ ወንድሞቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጊዜ እንደማያልፍባቸውና በዛሬው ጊዜም ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲወጡ እንደሚረዱ ገለጹለት። ሰውየው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 እና 2 ከወሰደ በኋላ እንዲህ አለ፦ “በዚህ አውደ ርዕይ ላይ እንዲህ ያለ ጠቃሚ መረጃ የያዙ መጻሕፍት አገኛለሁ ብዬ ፈጽሞ አልጠበቅኩም።”
አንዲት ሴት ወደ መጻሕፍት ማሳያው መጥታ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ትችል እንደሆነ ጠየቀች። የምትኖረው ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት አካባቢ ስለሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት የምትችልበት አጋጣሚ ጠባብ እንደሆነ ገለጸች። እህታችን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ከሰጠቻት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ስለምናስጠናበት ዝግጅት ነገረቻት። ሴትየዋ በጣም ተደስታ jw.org ላይ ያለውን ቅጽ በመሙላት መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምራት ሰው እንዲመደብላት ጠየቀች።
በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፈ ዲዬጎ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የjw.orgን አርማ ብዙ ሰዎች አይተውት የሚያውቁ ቢሆንም አንዳንዶቹ ስለ መልእክታችን እምብዛም እውቀት የላቸውም። በአውደ ርዕዩ ላይ የነበረው የጽሑፎች ማሳያ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜም ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ እንዲያስተውሉ እንደረዳቸው ይሰማኛል።”
በኢኳዶር የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እጅግ ጥንታዊ ሆኖም ለዘመናችን ጠቃሚ በሆነው መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጥበብ ያዘሉ ምክሮች ሌሎች እንዲያውቁ መርዳት በመቻላቸው በጣም ተደስተናል።—ምሳሌ 3:21