በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የኢኳዶር የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት

መስከረም 7, 2021
ኢኳዶር

የኢኳዶር የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን የአምልኮ ነፃነት አስከበረ

የኢኳዶር የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን የአምልኮ ነፃነት አስከበረ

ነሐሴ 24, 2021 የይሖዋ ምሥክሮች በኢኳዶር ታሪካዊ የፍርድ ቤት ድል ተቀዳጁ። የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ በኢምባቡራ ግዛት በምትገኘው የአገሬው ቀደምት ተወላጆች መኖሪያ በሆነችው በሳን ሁዋን ዴ ኢሉማን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ነፃነታቸው እንደጣሰ ገለጸ። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በመላው ኢኳዶር፣ በተለይም የአገሬው ቀደምት ተወላጆች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የአምልኮ ነፃነት መብትን ለማስከበር ያስችላል፤ በተጨማሪም በሌሎች አገሮች ለሚደረጉ ውሳኔዎችም እንደ መሠረት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።

በ2014 የአካባቢው መሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች ይዞታ ወደሆነ መሬት በመግባት የስብሰባ አዳራሹን ግንባታ በጉልበት ለማስቆም ሞከሩ። በተጨማሪም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለአምልኮ እንዳይሰበሰቡ እና ከቤት ወደ ቤት እንዳይሰብኩ ከለከሉ። ወንድሞቻችን ፍትሕ ለማግኘት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት። ሆኖም ሁለት ዳኞች የወንድሞቻችን ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳልተጣሰ በመግለጽ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ፈረዱ።

ወንድሞች በበታች ፍርድ ቤቶች ችግሩን ለመፍታት የቻሉትን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ጉዳዩን የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደሆነው ወደ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ወሰዱት። የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ፣ የበታች ፍርድ ቤቶች የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ሕጋዊ የአምልኮ ነፃነት መብት እንደጣሱ ገለጸ። በጉዳዩ ውስጥ እጃቸው ያለበት የአካባቢ መሪዎችና ዳኞች ሃይማኖታዊና ባሕላዊ መቻቻልን የሚመለከት ኮርስ እንዲወስዱ ታዘዙ። በተጨማሪም የአካባቢው መሪዎች “የተለያየ ሃይማኖትና ባሕል ያላቸው ሰዎች በሰላም አብረው እንዲኖሩ እንዲያደርጉ፣ በተለይም [የይሖዋ ምሥክሮችን] ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንዲያከብሩ” ተጠይቀዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ጠበቃ የሆነው ፊሊፕ ብረምሊ እንዲህ ብሏል፦ “የአገሬው ቀደምት ተወላጆች ያላቸው መብት ለባሕላቸው ጥበቃ ለማድረግ እንደሚያገለግል እናውቃለን፤ ሆኖም ይህን መብት ተጠቅሞ የማንኛውንም ዜጋ መሠረታዊ መብት ለመጣስ መሞከር ተገቢ አይደለም።”

በሳን ሁዋን ዴ ኢሉማን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ፍርድ ቤቱ ላስተላለፈው ውሳኔ አመስጋኞች ናቸው።

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የአምልኮ ነፃነታቸውን የሚያስከብር የፍርድ ቤት ድል በማግኘታቸው ‘የይሖዋን እጅ’ ማየት ችለናል፤ ለዚህም በጣም ደስተኞች ነን።—ምሳሌ 21:1

በሳን ሁዋን ዴ ኢሉማን የሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ