በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጋቢት 9, 2022
ኢኳዶር

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ኪምቦራዞ እና ኢምባቡራ በተባሉት የኪችዋ ቀበልኛዎች ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ኪምቦራዞ እና ኢምባቡራ በተባሉት የኪችዋ ቀበልኛዎች ወጣ

የኢኳዶር ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አለን ኮስታ ቅዳሜ፣ መጋቢት 5, 2022 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የኪችዋ ቋንቋ ቀበልኛዎች በሆኑንት በኪምቦራዞ እና በኢምባቡራ መውጣቱን አብስሯል። ኪምቦራዞ እና ኢምባቡራ በኢኳዶር የሚነገረው የኪችዋ ቋንቋ ዋነኛ ቀበልኛዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱሶቹ የወጡት በታተመና በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ሲሆን ፕሮግራሙ በቀጥታ ስርጭት ለአስፋፊዎች ተላልፏል።

በአንዲስ ተራሮች የሚገኘው የኢምባቡራ የርቀት ትርጉም ቢሮ። ከዋና ከተማው ከኪቶ በስተ ሰሜን 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለው በኦታቫሎ ይገኛል

አብዛኞቹ የኪችዋ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩት ከባሕር ጠለል በላይ ከ2,700 እስከ 3,700 ከፍታ ላይ በሚገኙት የአንዲስ ተራሮች ላይ ነው። ማኅበረሰቡ በእጅጉ ይቀራረባል፤ እንዲሁም ለጋስ፣ ታታሪና እንግዳ ተቀባይ በመሆን የሚታወቅ ነው። ብዙዎች በፈጣሪ ያምናሉ፤ ለመጽሐፍ ቅዱስም ጥልቅ አክብሮት አላቸው።

በ1990ዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ኢኳዶር የሚገኙትን የኪችዋ ቋንቋዎች በመቀላቀል ጽሑፎችን መተርጎም ጀመሩ። ይሁንና ከኪችዋ ተናጋሪዎች መካከል ለመንግሥቱ ምሥራች አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። በዚህም የተነሳ ውጤታማ መሆን የሚቻለው በእያንዳንዱ ቀበልኛ ጽሑፎች ከተተረጎሙ እንደሆነ ወንድሞች ማስተዋል ቻሉ።

የኪምቦራዞ የርቀት ትርጉም ቢሮ ከኪቶ በስተ ደቡብ 208 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለው በሪዮባምባ ይገኛል

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ አስፋፊዎች የትርጉም ሥራዎቹን ገምግመው ሐሳብ በመስጠት ለኪችዋ የትርጉም ቡድኖች እገዛ አበርክተዋል። የኪምቦራዞን መጽሐፍ ቅዱስ በመተርጎም የተካፈለ አንድ ተርጓሚ ቋንቋው በተለያየ መንገድ መነገሩ ስላስከተለው ተፈታታኝ ሁኔታ ሲናገር “እነሱ የሰጡን ሐሳብ ሚዛናዊ እንድንሆን ረድቶናል” ብሏል። በኢምባቡራ ቡድን ውስጥ የሚገኝ አንድ ተርጓሚ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ አመራር አልተለየንም፤ ይህም ይሖዋ ሁሉም ሰው ቃሉን ማወቅና መረዳት እንዲችል እንደሚፈልግ በግልጽ የሚያሳይ ነው።”

ኪችዋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች የሚያድነውን’ አምላካችንን ይሖዋን ሲያገለግሉ እነዚህ ሁለት መጽሐፍ ቅዱሶች በእጅጉ እንደሚጠቅሟቸው እርግጠኞች ነን።—1 ጢሞቴዎስ 4:10