በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ተስፋፅዮን ገብረሚካኤል ኤርትራ ውስጥ ላለፉት 11 ዓመታት ታስሮ ቆይቷል

ጥቅምት 26, 2022
ኤርትራ

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ነፃነት ኮሚሽን የ80 ዓመቱ ኤርትራዊ የይሖዋ ምሥክር ከእስር እንዲፈታ ጠየቀ

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ነፃነት ኮሚሽን የ80 ዓመቱ ኤርትራዊ የይሖዋ ምሥክር ከእስር እንዲፈታ ጠየቀ

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ነፃነት ኮሚሽን፣ ላለፉት 11 ዓመታት በእስር የቆየው የወንድም ተስፋፅዮን ገብረሚካኤል ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገለጸ። የኮሚሽኑ ድረ ገጽ “በአሁኑ ወቅት በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ተስፋፅዮን ገብረሚካኤል ከዕድሜው አንጻር እስር ቤት መቆየቱ በጤናውና በደህንነቱ ላይ የሚፈጥረው ስጋት ያሳስባል” ብሏል። ጥቅምት 7, 2022 ኮሚሽነር ፍሬድሪክ ዴቪ ወንድም ተስፋፅዮን እንዲፈታ በይፋ ጠይቀዋል።

ሐምሌ 20, 2011 ወንድም ተስፋፅዮን ስለ እምነቱ ለሌሎች እየተናገረ ባለበት ወቅት ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር አዋሉት። ወንድም ተስፋፅዮን እዚያው ኤርትራ የተወለደ ቢሆንም ዜግነቱን ተነጥቋል፤ እንደሚታወቀው ከ1994 አንስቶ የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ዜግነታቸውን እንዲነጠቁ ወስኗል።

ወንድም ተስፋፅዮን የይሖዋ ምሥክር የሆነው ጥር 1971 ነው። በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታወቀው አፍቃሪ፣ ደግና ሰላማዊ አባት በመሆኑ ነው። በ1974 ከለምለም ጋር ተጋቡ። እሷም የይሖዋ ምሥክር ነች። አራት ልጆችና አምስት የልጅ ልጆች አሏቸው።

እህት ለምለም እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ እስር ቤት ሆኖ ቢታመም የሚለው ጉዳይ ያስጨንቀኛል፤ ፍቅሩና አጋርነቱም ይናፍቀኛል። ሆኖም ይሖዋ እንደሚንከባከበው እርግጠኛ ነኝ። ታማኝነቱና ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ያለው ቆራጥነት ያስደንቀኛል። ቤተሰባችን የገጠመው ሁኔታ ከባድ ቢሆንም በመክብብ 10:4 ላይ ማሰላሰሌ እንድረጋጋ ይረዳኛል።”

ኤርትራ ከ1991 አንስቶ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የከፈተችው የስደት ዘመቻ አሁንም አላባራም። እርግጥ ነው፣ ከታኅሣሥ 2020 እስከ የካቲት 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ 32 የይሖዋ ምሥክሮች በቅድመ ሁኔታ ከእስር ተፈትተዋል፤ ሆኖም አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ 20 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሉ። ሁሉም የታሰሩት ላልተወሰነ ጊዜ ነው። አቤቱታ የሚያቀርቡበት ወይም ይግባኝ የሚሉበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ አሠራር በአገሪቱ ባለመኖሩ እስራታቸው ከዕድሜ ይፍታህ ፍርድ አይተናነስም።

ትላልቅ የሚባሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት፣ ኤርትራ የምትፈጽመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በተደጋጋሚ ሲያወግዙ ቆይተዋል፤ የኤርትራ መንግሥት ለጉዳዩ እልባት እንዲያበጅም ጠይቀዋል። እንዲያውም የተ.መ.ድ. የኤርትራ የሰብዓዊ መብቶች አጣሪ ኮሚሽን በ2016 ባወጣው መግለጫ ላይ የኤርትራ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያደረሱት ስደት “በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል” ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል ገልጿል።

አሁንም በእስር ላይ የሚገኘው የወንድም ተስፋፅዮን ሁኔታ፣ የኤርትራ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ሲተገብር የቆየውንና ለአረጋውያን እንኳ ርኅራኄ የሌለውን ፖሊሲ የሚያሳይ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ከ2011 ወዲህ አራት የይሖዋ ምሥክሮች እስር ቤት ሳሉ ሕይወታቸው አልፏል፤ ሦስት በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ደግሞ ታስረው በደረሰባቸው እንግልት የተነሳ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ሞተዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች የባለሥልጣናቱን ይሁንታ አላገኙም።

አሁንም በግፍ ለታሰሩት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንጸልያለን። ይሖዋ እንደ ቀድሞው ሁሉ ወደፊትም እንደሚንከባከባቸው አንጠራጠርም።—ዕብራውያን 13:3