ግንቦት 31, 2019
እስራኤል
በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ወደ ቴል አቪቭ መጉረፋቸው በእስራኤል የአደባባይ ምሥክርነት በስፋት እንዲሰጥ መንገድ ከፈተ
በእስራኤል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከግንቦት 10 እስከ 19 ባሉት ቀናት ቴል አቪቭ ውስጥ በአደባባይ ምሥክርነት በስፋት ለመካፈል የተደራጀ ጥረት አድርገዋል። ይህን የአደባባይ ምሥክርነት እንዲያደራጁ ያነሳሳቸው፣ በከተማዋ ውስጥ በሚደረጉ የተለያዩ ባሕላዊ ዝግጅቶች የተነሳ የጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩ ነው። ለምሳሌ፣ ከግንቦት 14 እስከ 18 ባሉት ቀናት ቴል አቪቭ ውስጥ በተካሄደው ዩሮቪዥን በተባለ የሙዚቃ ውድድር ላይ አሥር ሺህ ገደማ የሚሆኑ ጎብኚዎች ተገኝተው ነበር።
የአደባባይ ምሥክርነቱን በማደራጀቱ ሥራ የተካፈለው ወንድም ጄናዲ ኮሮቦቭ እንዲህ ብሏል፦ “በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች በሙዚቃ ዝግጅቱ ላይ ለመገኘት ወደ ቴል አቪቭ እንደሚመጡ ስናውቅ፣ የአደባባይ ምሥክርነታችንን ለማስፋት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ እንዳገኘን ተሰማን። በመላው እስራኤል ከሚገኙ 22 ጉባኤዎች የተውጣጡ 168 አስፋፊዎች በዚህ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኞች በመሆናቸው በጣም ተደስተናል።”
ወንድሞች በየቀኑ ከጠዋቱ 3:00 እስከ ምሽቱ 3:00 ድረስ የጽሑፍ ጋሪዎችን በስምንት የተለያዩ ቦታዎች ላይ አቁመው ነበር። ጎብኚዎቹ የመጡት ከብዙ አገራት በመሆኑ በአሥር የተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች በጋሪዎቹ ላይ እንዲቀመጡ ተደርጎ ነበር። ጽሑፎቹ በሩሲያኛ፣ በስፓንኛ፣ በቻይንኛ፣ በአረብኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በዕብራይስጥ፣ በጀርመንኛ፣ በጃፓንኛ፣ በጣሊያንኛ እና በፈረንሳይኛ የተዘጋጁ ናቸው።
በእስራኤል የተደረገው ይህ ተጨማሪ ጥረት ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ሙሉ እምነት አለን። ወንድሞች በዚህ ሥራ መካፈላቸው የይሖዋ ሕዝቦች እሱን “ሁልጊዜ” እንደሚያወድሱት የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—መዝሙር 34:1, 2