ሚያዝያ 28, 2022
እስራኤል
ናዚዎች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስላደረሱት ስደት የሚያሳይ አውደ ርዕይ በእስራኤል ተከፈተ
የይሖዋ ምሥክሮች ከናዚዎች ስደት ቢደርስባቸውም በድፍረት መጽናታቸውን የሚያሳይ አውደ ርዕስ መጋቢት 7, 2022 በእስራኤል ተከፈተ። አውደ ርዕዩ የሚካሄደው በምዕራብ ገሊላ በሚገኘው ጌቶ ፋይተርስ ሃውስ ሙዚየም ውስጥ ባለው የሰብዓዊነት ትምህርት ማዕከል ውስጥ ሲሆን በአረብኛ፣ በእንግሊዝኛና በዕብራይስጥ ይቀርባል። አውደ ርዕዩ እስከ መጋቢት 2023 ድረስ ይካሄዳል። አውደ ርዕዩ በሚዘጋጅበት ወቅት ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ከ50 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ከሙዚየሙ ሠራተኞች ጋር በመተባበር እንደ ታሪካዊ ምርምር፣ ግራፊክ ዲዛይን እና ትርጉም ባሉት ሥራዎች ተካፍለዋል።
የአውደ ርዕዩ ርዕስ “Wedontdothat” የሚል ሲሆን ርዕሱ የተወሰደው አንድ የጀርመን መከላከያ አባል ለወንድም ዮአኪም አልፈማን ከሰጠው ቅጽል ስም ነው፤ ትርጉሙም “እኛ እንዲህ አናደርግም” የሚል ነው። a ዮአኪም ከባድ ጫና ቢደርስበትም፣ ቢደበደብም እንዲሁም ብቻውን ቢታሰርም በጀርመን ጦር ሠራዊት ውስጥ ለመሠልጠን ፈቃደኛ አልሆነም፤ “እኛ እንዲህ አናደርግም” ይል ነበር። መሣሪያ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ከጊዜ በኋላ ወደ ማጎሪያ ካምፕ ተልኳል። አውደ ርዕዩን ያደራጁት ያራ ጌለር የተባሉት ሴት እንዲህ ብለዋል፦ “በተለያየ ምክንያት ከተገደሉት አይሁዳውያን በተጨማሪ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ተገድለዋል። . . . እያንዳንዱ ቡድን የየራሱ ታሪክ አለው።”
ስለ ሆሎኮስት በሰፊው ያጠኑትና የኦሽዊትዝ የታሪክ ምሁር የሆኑት ዶክተር ጊዲየን ግሪፍ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያቀረቡ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን እንደካዱ በሚገልጽ ወረቀት ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ ስላለመሆናቸው ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “[የይሖዋ ምሥክሮች] በቀላሉ ነፃነታቸውን ማግኘት ይችሉ ነበር፤ ወረቀቱ ላይ ለመፈረም ከአንድ ደቂቃ በላይ አይወስድም። ይህም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ በሆነ ወቅትም ጭምር በንግግራቸውም ሆነ በድርጊታቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርት የሚከተሉ ቡድኖች እንዳሉ ያሳያል። በመሆኑም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች መናገር፣ እነሱን ማስታወስ፣ ስለ እነሱ ማወቅና ስለ እነሱ ማስተማር ተገቢ ነው።”
በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የተገኘች በእስራኤል ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የምታገለግል እህት እንዲህ ብላለች፦ “እስራኤል ውስጥ ለሕዝብ ክፍት የሆነ እንዲህ ዓይነት አውደ ርዕይ በመካሄዱ እንባ ተናነቀኝ። . . . የሙዚየሙ ሠራተኞች ከመድረክ ሆነው በዕብራይስጥ ‘የይሖዋ ምሥክሮች’ ሲሉ መስማቴ የማይረሳ ትዝታ ፈጥሮብኛል። በእርግጥም በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት የይሖዋ ስም ተከብሯል።”
ይህን አውደ ርዕይ የሚያዩ ሰዎች በናዚ ጀርመን የነበሩ ወንድሞቻችን ስላሳዩት ድፍረትና እምነት የመማር አጋጣሚ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነን። ወንድሞቻችን የተዉት የታማኝነት ምሳሌ በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ‘ሩጫቸውን በጽናት እንዲሮጡ’ ያነሳሳቸዋል።—ዕብራውያን 12:1