በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የካቲት 6, 2024
ኩባ

የማቴዎስ እና የማርቆስ መጻሕፍት በኩባ ምልክት ቋንቋ ወጡ

የማቴዎስ እና የማርቆስ መጻሕፍት በኩባ ምልክት ቋንቋ ወጡ

ጥር 20, 2024 ሃቫና፣ ኩባ ውስጥ በጓናባኮዋ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ የማቴዎስ እና የማርቆስ መጻሕፍት በኩባ ምልክት ቋንቋ መውጣታቸው ይፋ ሆኗል። መጻሕፍቱ ወዲያውኑ jw.org ላይ ለተጠቃሚዎች ተለቅቀዋል።

ኩባ ውስጥ 53,000 መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዳሉ ይገመታል። ምሥራቹን በአገሪቱ ላሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ለማድረስ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ልዩ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በ2011 በኩባ ምልክት ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ተዘጋጁ። በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ባሉ 28 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና 10 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 756 ወንድሞችና እህቶች አሉ።

አንዲት እህት፣ መስማት የተሳነው አንድ ወንድም አዲስ የወጡትን መጻሕፍት ስልኩ ላይ እንዲያወርድ ስታግዘው

በኩባ ምልክት ቋንቋ የማቴዎስ እና የማርቆስ መጻሕፍት ተተርጉመው ሲወጡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። አንዲት እህት እንዲህ ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፦ “ማርቆስ 7:32-37 ላይ ኢየሱስ መስማት የተሳነውን ሰው እንደፈወሰው የሚገልጸው ታሪክ የተተረጎመበት መንገድ በጣም ሕያው ነው፤ እኔ ራሴ ታሪኩ ላይ ያለሁ ያህል ተሰምቶኛል። በጣም ነው ልቤን የነካው። በአዲሱ ዓለም የሚኖረን ሕይወት ይበልጥ ሕያው እንዲሆንልኝ አድርጓል። ከልብ አመሰግናለሁ።”

ይህን መንፈሳዊ ስጦታ ያገኙ ወንድሞቻችንን ደስታ እኛም እንጋራለን፤ እነዚህ መጻሕፍት የኩባ ምልክት ቋንቋን የሚጠቀሙ ሌሎች ብዙ ሰዎች ይሖዋን ‘በሙሉ ልብ፣ ነፍስ እና አእምሮ’ እንዲወዱት ያደርጋሉ የሚል ሙሉ እምነት አለን።​—ማርቆስ 12:30