ታኅሣሥ 23, 2021
ኪርጊስታን
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ኪርጊስታን የይሖዋ ምሥክሮችን መብት እንደጣሰች ገለጸ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ (CCPR) ኪርጊስታን የይሖዋ ምሥክሮችን መሠረታዊ መብት እንደጣሰች በመግለጽ ድርጊቱን አውግዟል፤ የኮሚቴው 15 አባላት በአገሪቱ በሦስት የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን በነፃነት የማካሄድ ሰብዓዊ መብታቸው እንደተጣሰባቸው በሙሉ ድምፅ ተስማምቷል። ኮሚቴው ሰባት ገጽ ባለው ውሳኔው ላይ ኪርጊስታን ለይሖዋ ምሥክሮች “ተመጣጣኝ ካሳ” እንድትሰጥና “ወደፊት ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እንዳይኖሩ ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ እንድትወስድ” አዘዋል። ኮሚቴው የይሖዋ ምሥክሮችን መብቶች በመጣሷ ኪርጊስታንን ሲያወግዝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው።
ኪርጊስታን ውስጥ በተወሰነ አካባቢ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ያገኙት በ1993 ሲሆን ከ1998 አንስቶ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል። በመሆኑም በመላው አገሪቱ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በርከት ላሉ ዓመታት የአምልኮ ነፃነት ነበራቸው። ሆኖም ከአሥር ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ የአገሪቱ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ኮሚቴ (SCRA) ኦሽ፣ ናሪን እና ጃላል-አባድ በተባሉ ደቡባዊ አካባቢዎች ላሉ ሦስት አዳዲስ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ተቋማት እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። በአካባቢው ያሉ ወንድሞች በተደጋጋሚ ማመልከቻ ቢያስገቡም ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ኮሚቴው አቋም በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈሉ፣ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርጉና የአምልኮ ቦታዎችን እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ሆኗል። የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው ኪርጊስታን በእነዚህ ሦስት አካባቢዎች ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ በእምነታቸው ምክንያት መድልዎ ፈጽማለች የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው በዚህ ምክንያት ነው።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው የኪርጊስታን ባለሥልጣናት “ወደፊት ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እንዳይኖሩ ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ” እንደሚወስዱ ይጠብቃል። ኪርጊስታን ይህን ውሳኔ ተግባር ላይ ለማዋል እያደረገች ስላለችው ጥረት እንድታሳውቅ 180 ቀናት ተሰጥቷታል።
የኪርጊስታን ባለሥልጣናት ከኮሚቴው ውሳኔ ጋር በመስማማት በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በነፃነት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያካሂዱ ይፈቅዳሉ ወይስ አይፈቅዱም የሚለውን ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። ሆኖም በፎረም 18 ውስጥ ያሉት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተሉ ቆይተዋል፤ በተጨማሪም የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ኮሚቴው “የተባበሩት መንግሥታት በ2019 ያስተላለፈውን ተመሳሳይ ውሳኔ ችላ እንዳለ” ሪፖርት አድርገዋል።
ኪርጊስታን የተባበሩት መንግሥታትን ውሳኔ ተግባራዊ አደረገችም አላደረገች ይሖዋ በኪርጊስታን ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያሉበትን ሁኔታ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እርግጠኞች ነን። (መዝሙር 37:18) በሰማይ ያለው አፍቃሪ አባታችን የምናሳየውን ታማኝነትና ድፍረት መባረኩን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—መዝሙር 37:28