የካቲት 13, 2020
ካሜሩን
የካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ ወደ ሌላ ቦታ ተዛወረ
ጥር 20, 2020 የካሜሩን ቤቴል ቤተሰብ አባላት በዱዋላ ከተማ ሰሜን ምሥራቃዊ ክፍል ባለው በሎግበሱ ወደሚገኘው አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ገብተዋል። በአሁኑ ወቅት 59 ወንድሞችና እህቶች በአዲሱ ሕንፃ ውስጥ ይኖራሉ፤ የሚሠሩትም እዚያው ነው፤ ከዚህም ሌላ 71 ወንድሞችና እህቶች በተመላላሽነት ያገለግላሉ።
የቀድሞው የካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኘው በዱዋላ ከተማ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው በቦናቤሪ ነበር። ለ23 ዓመታት በድርጅታችን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ከተነሳ በኋላ በ1993 ወንድሞቻችን በቦናቤሪ የሚገኙትን ሕንፃዎች አድሰው መጠቀም ጀመሩ። ከ1993 ወዲህ በካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች ቁጥር ከ19,268 ተነስቶ 52,000 አልፏል፤ እንዲሁም የትርጉም ሥራ የሚከናወንባቸው ቋንቋዎች 29 ደርሰዋል። እንዲህ ያለው እድገት ወንድሞቻችን ሰፋ ያለ ቅርንጫፍ ቢሮ አንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል። a
አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ የጎብኚዎች ማዕከል ይኖረዋል፤ ማዕከሉ በ2020 መጨረሻ ላይ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። የጎብኚዎች ማዕከሉ የቅርንጫፍ ቢሮውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ እንዲሁም የኢኳቶሪያል ጊኒን፣ የካሜሩንንና የጋቦንን የስብከት ሥራ ታሪክ የሚያወሳ አውደ ርዕይ ይኖረዋል።
የካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን አቶህ እንዲህ ብሏል፦ “ወደዚህ አዲስ ሕንፃ ስንዘዋወር ዓይናችንን ማመን ከብዶን ነበር። በዚህ ግሩም የሥራ ቦታ ላይ ለይሖዋ ምርጣችንን ለመስጠት ቆርጠናል። ይሖዋ ብዙ ነገር አድርጎልናል፤ እኛም ስላደረገልን ነገር ስናስብ ልባችን በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል።”—መዝሙር 145:7
a ቅርንጫፍ ቢሮው ከካሜሩን በተጨማሪ በኢኳቶሪያል ጊኒ እና በጋቦን የሚከናወነውን የስብከት ሥራ ይኸውም የ667 ጉባኤዎችን እንቅስቃሴ በበላይነት ይከታተላል