ነሐሴ 15, 2022
ካሜሩን
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጽሐፍት በቦውሉ ቋንቋ ወጣ
ነሐሴ 6, 2022፣ የካሜሩን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጊሌስ ኤምባ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቦውሉ ቋንቋ መውጣቱን አስቀድሞ በተቀዳ ፕሮግራም አማካኝነት አበሰረ። ፕሮግራሙ ለአስፋፊዎች የተላለፈ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሱ የወጣው በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ነው። የታተመው ቅጂ በ2023 ይወጣል።
በዚህ ቋንቋ የተዘጋጁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ማግኘት የሚቻል ቢሆንም ዋጋቸው ውድ ነው። ከእነዚህ ትርጉሞች አንዳንዶቹ ጥንታዊ ቃላትን የሚጠቀሙ ሲሆን የአምላክንም ስም አውጥተውታል። ከዚህም በተጨማሪ በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኙ ብዙ ሐሳቦችን በትክክል አያስተላልፉም። ለምሳሌ አንዳንድ የቦውሉ ትርጉሞች “የአምላክ መንግሥት” የሚለውን አገላለጽ “የአምላክ ጎሳ፣” “የአምላክ ወገን” ወይም “የአምላክ አገር” ብለው ተርጉመውታል። ይህ አዲስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም “መንግሥት” የሚለውን አገላለጽ ስለሚጠቀም የአምላክ መንግሥት ይሖዋ ያቋቋመው አገዛዝ መሆኑን በቀላሉ ማስረዳት ይቻላል።
አንድ የትርጉም ቡድኑ አባል እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለሌሎች እውነተኛ የሆነና ተአማኒነት ያለው ትምህርት ለማስተላለፍ ያስችለናል።”
በቦውሉ ቋንቋ የተዘጋጀው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ” ሰዎችን መርዳታቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚያግዛቸው እንተማመናለን።—ማቴዎስ 5:3