ኅዳር 26, 2021
ካናዳ
በምዕራብ ካናዳ የጣለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ አስከትሏል
ከኅዳር 13 እስከ 15, 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ በምዕራብ ካናዳ በሚገኙ የብሪቲሽ ኮሎምቢያ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ጥሏል። ሃያ አካባቢዎች እስካሁን ድረስ ታይቶ የማያውቅ ከፍተኛ ዕለታዊ ዝናብ ያስመዘገቡ ሲሆን በአንዳንዶቹ አካባቢዎች በሦስቱ ቀናት ውስጥ ብቻ ከ250 ሚሊሜትር በላይ ዝናብ ጥሏል። ዝናቡ ያስከተለው ጎርፍና የመሬት መንሸራተት መንገዶች እንዲዘጉ፣ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉና መንገደኞች ወዳሰቡበት ቦታ እንዳይደርሱ ምክንያት ሆነዋል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
ከወንድሞቻችን መካከል የአካል ጉዳት የደረሰበት የለም
144 አስፋፊዎች መኖሪያቸውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል
ቢያንስ 35 ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
የካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁሟል
ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ወንድሞችና እህቶች ከአደጋው ቀጠና ውጭ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዘመዶቻቸውና ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋ በመሄድ ጊዜያዊ መጠለያ አግኝተዋል
የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች አደጋው በደረሰበት አካባቢ ያሉ ቤተሰቦችን እያጽናኑ ነው
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ከአካባቢ ንድፍና ግንባታ ቡድን ጋር በመተባበር ባለሥልጣናቱ ፈቃድ ወደሰጡባቸው አካባቢዎች በመሄድ በቤቶች ላይ የደረሰውን ጉዳትና ቤቶቹን ለማደስ መደረግ ያለበትን ነገር እየገመገመ ነው
የእርዳታ እንቅስቃሴው በሙሉ የሚካሄደው ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የወጡትን የደህንነት ደንቦች ባገናዘበ መልኩ ነው
አደጋው በደረሰበት አካባቢ ካሉት የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች መካከል አብዛኞቹ ከሦስት ወራት በፊት ማለትም ነሐሴ 2021 ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሰደድ እሳት ምክንያት ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ታዘው ነበር። ከባድ የአየር ሁኔታዎችና የተፈጥሮ አደጋዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩ ባሉበት በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች የአደጋ ጊዜ ሻንጣና ምግብ እንዲያዘጋጁ የተሰጣቸውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው ጥቅም እያገኙ ነው።
አደጋዎች የሚከሰቱበት ፍጥነትም ሆነ የሚያስከትሉት ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሄድም በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ ያለን እምነት ፈጽሞ አይናወጥም።—ዕንባቆም 3:17, 18