ጥቅምት 28, 2022
ካናዳ
በካናዳው “የብዙ ዓሦች መገኛ” የስብሰባ አዳራሽ ተገነባ
ካናዳ ውስጥ በኢካሉዊት፣ ኑናቩት የሚገኘው የኢካሉዊት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የመጀመሪያ የስብሰባ አዳራሹን አስገንብቷል። የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች፣ 50 ወንበሮች ያሉትን የስብሰባ አዳራሽ ገንብተው ያጠናቀቁት ጥቅምት 14, 2022 ነው። ይህ መሰብሰቢያ በካናዳ የመጨረሻው ሰሜናዊ ጫፍ ላይ የሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ነው። የኢካሉዊት ጉባኤ የተቋቋመው በ2010 ሲሆን ስብሰባዎችን የሚያደርገው በትምህርት ቤት ጂምናዚየም ውስጥ ነበር።
ይህ የግንባታ ፕሮጀክት ከባድ የሎጂስቲክስ ችግሮች ነበሩበት፤ ደግሞም በወረርሽኙ ምክንያት ግንባታው ለሁለት ዓመት ተጓትቷል። ኢካሉዊት “የብዙ ዓሦች መገኛ” የሚል ትርጉም አለው፤ በባፊን ደሴት፣ በፍሮቢሸር የባሕር ወሽመጥ ላይ የሚገኝ ቦታ ነው። ወደዚያ መሄድ የሚቻለው በአየር ወይም በባሕር ትራንስፖርት ብቻ ነው። ከዚህም ሌላ የግንባታ ቁሳቁሶችን በአካባቢው ማግኘት አይቻልም። በመሆኑም የግንባታ መሣሪያዎችንና ግብዓቶችን በባሕር መላክ ግድ ነበር። በተጨማሪም ከአየሩ ጠባይ የተነሳ ግንባታ ማከናወን የሚቻለው ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ብቻ ነው።
በመጀመሪያ ኦንታሪዮ በሚገኝ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ 127 ሜትሪክ ቶን የሚመዝኑ የግንባታ መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ተሰባሰቡ። ከዚያም በ12 የባሕር ኮንቴነሮችና በሦስት ትላልቅ የመርከብ ሣጥኖች ተጭነው በሞንትሪያል፣ ኩዊቤክ ወዳለ ወደብ ተወሰዱ። ከዚያ ደግሞ በሴንት ሎውረንስ የባሕር መንገድ በኩል ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ፣ በመጨረሻም ወደ ፍሮቢሸር የባሕር ወሽመጥ ተላኩ። በዚህ የባሕር ወሽመጥ ትላልቅ መርከቦችን የሚያስተናግድ ወደብ ስለሌለ ኮንቴነሮቹ ጠፍጣፋ መጫኛ ያላቸው ጀልባዎች ላይ ተጫኑ። ከዚያም ጎታች ጀልባዎች ዕቃ የጫኑትን ጀልባዎች እየጎተቱ ጥልቀት ወደሌለው የባሕሩ አካባቢ ወሰዷቸው። ከዚያም ሞገዱ የሚቀንስበት ሰዓት ላይ ጭነት አውራጅ መኪናዎች ኮንቴነሮቹን አንስተው ወደ ባሕሩ ዳርቻ አመጧቸው።
የስብሰባ አዳራሹ ንድፍ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኒክ የተተገበረበት ነው። ምክንያቱም ሕንፃው በረዶ ሲጋገርና ሲቀልጥ ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳትና በኢካሉዊት የሚገኘውን በጣም አስቸጋሪ የአየር ጠባይ መቋቋም የሚችል መሆን አለበት፤ ክረምት ላይ የቅዝቃዜው መጠን በአማካይ ከዜሮ በታች 30 ዲግሪ ሴልሸስ ነው።
ከስድስት ግዛቶች የተውጣጡ 40 ገደማ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በሥራው ለመካፈል ሲሉ ወደዚህ ገለልተኛ አካባቢ መጥተዋል። ከፈቃደኛ ሠራተኞቹ አንዱ የሆነው ወንድም ጄሰን ማክግሪጎር እንዲህ ብሏል፦ “የግንባታ ቁሳቁሶችን ወደ ሰሜናዊ ጫፍ ማጓጓዝም ሆነ የዕቃ አቅርቦት እጥረት፣ የይሖዋ ፈቃድ እንዳይፈጸም እንቅፋት የሆነ አንድም የሎጂስቲክስ ችግር አልነበረም። የሥራውን ሂደት በየቀኑ መመልከት እምነት የሚያጠናክር ነበር።”
“በብዙ ዓሦች መገኛ” የሚኖሩት የካናዳ ወንድሞቻችን አዲስ የስብሰባ አዳራሽ በማግኘታቸው በጣም ደስ ብሎናል፤ “ሰው አጥማጆች” በመሆን በሚያከናውኑት አስፈላጊ ሥራ እንደሚያግዛቸውም እምነታችን ነው።—ማቴዎስ 4:19